የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 31

31
የኢያሱ በሙሴ እግር መተካት
1ሙሴም ወጥቶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ፤ 2#ዘኍ. 20፥12።“እነሆ፤ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ልወጣና ልገባ አልችልም፤ ጌታም ‘ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል፤ 3ጌታ አምላክህም ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ ጌታ እንደ ተናገረው ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል። 4#ዘኍ. 21፥21-35።ጌታ የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው እነዚህንም ያጠፋቸዋል። 5ጌታ እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኳችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ። 6ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። ጌታ አምላክህም ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።” 7ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “ጌታም ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፥ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን። 8#ኢያ. 1፥5፤ ዕብ. 13፥5።ጌታ ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቁረጥ።”
ሕጉ በየሰባት ዓመት መነበብ እንዳለበት
9ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፥ የጌታን የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፥ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ። 10#ዘዳ. 15፥1፤2፤ ዘዳ. 16፥13-15።ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፥ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፥ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፥ 11እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በጌታህ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ። 12ይሰሙና ጌታ አምላካችሁንም መፍራት ይማሩ ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፥ ሴቶችን፥ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ። 13ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና ጌታ አምላካችሁንም መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።”
እግዚአብሔር ለሙሴና ለኢያሱ የሰጣቸው መመሪያ
14ጌታ ሙሴን፥ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቧል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ። 15ጌታም በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።
16ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ። 17በዚያች ቀን እቀጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፥ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ። 18ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፥ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ።
19“እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ። 20ወተትና ማር ወደምታፈሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፥ ከበለጸጉም በኋላ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ። 21ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል። በዘራቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደ ማልሁላቸው ምድር ሳላስገ ባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳን አስቀድሜ ዐውቃለሁ።”
22ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው።
23 # ዘኍ. 27፥23፤ ኢያ. 1፥6። ጌታም ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፥ “በርታ፤ ደፋር ሁን፤ የእስራኤልን ልጆች በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ታስገ ባቸዋለህና፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠው።
24ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ሕግ ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ፥ 25የጌታን የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 26“በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖር ዘንድ በጌታ በእግዚአብሔር የኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖራል፤ 27እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፥ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በጌታ ላይ ዐምፃችኋል፥ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል? 28ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፥ 29እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በጌታ ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፥ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ስለምታስቆጡት በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።”
የሙሴ መዝሙር
30ሙሴም የዚህን መዝሙር ቃል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ፥ ለተሰበሰበው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በጆሮአቸው እንዲህ ሲል አሰማ፦

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ