ኦሪት ዘፀአት 10
10
8. የአንበጣ መንጋ
1ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እኔ ልቡንና የአገልጋዮቹን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው ምልክቶቼን እንዳሳይ ነው። 2ይህም በልጅህና በልጅ ልጅህ ጆሮ እንድትነግርና ግብፃውያንን እንዴት እንዳሞኘኋቸው፥ በመካከላቸው ያስቀመጥኩት ምልክቶቼም ጌታ እንደሆንኩ እንድታውቁ ነው።” 3ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እንዲህም አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘በፊቴ እራስህን ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 4ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ እኔ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤ 5የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታል፥ ማንም ምድሩን ማየት አይችልም፤ ከበረዶውም ተርፎ የቀረላችሁን ሁሉ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም በሜዳ ያለ ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤ 6ቤቶችህም የአገልጋዮችህም ቤቶች ሁሉ የግብጽንም ቤቶች ሁሉ ይሞሉታል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ አላዩም።’” ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 7የፈርዖንም አገልጋዮች፦ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? ጌታ አምላካቸውን እንዲያገለግሉት ወንዶቹን ልቀቃቸው፥ ግብጽስ እንደ ጠፋች ገና አላወቅህምን?” አሉት። 8ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን አመጡአቸው፦ “ሂዱ፥ ጌታ አምላካችሁን አገልግሉ፥ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። 9ሙሴም፦ “ወጣቶቻችን፥ ሽማግሌዎቻችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፥ በጎቻችንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ የጌታን በዓል እናደርጋለንና” አለ። 10እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን እናንተንና ልጆቻችሁን እለቅቃለሁ፥ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ። 11እንዲህ አይሆንም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱና ጌታን አገልግሉ፥ የጠየቃችሁት ይህንን ነውና።” ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው።
12ጌታም ሙሴን፦ “አንበጣዎቹ በግብጽ ምድር ላይ እንዲመጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ” አለው። 13ሙሴም በግብጽ ምድር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ ጌታም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ በነጋም ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ። 14#ራእ. 9፥2፤3።አንበጣዎችም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብጽም አገር ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፥ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ ያለ አይሆንም። 15የምድሩንም ፊት ሸፈኑት ምድሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር በዛፉ ላይም በቡቃያው ላይም በግብጽ ምድር ሁሉ አልቀረም። 16ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠራና እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ አምላካችሁንና እናንተን በደልሁ፤ 17አሁን እንግዲህ አንድ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንን ሞት ከእኔ እንዲያነሣልኝ ብቻ ጌታ አምላካችሁን ለምኑልኝ።” 18እርሱም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ ጌታም ፀለየ። 19ጌታም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን መለሰ፥ አንበጣዎቹንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ ስንኳ አንበጣ በግብጽ አገር አልቀረም። 20ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።
9. ጨለማ
21 #
ጥበ. 17፥1-21። ጌታም ሙሴን፦ “በግብጽ ምድር ላይ ጨለማ እንዲሆን፥ ማንም ሰው የሚያውቀው ጨለማ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ” አለው። 22#መዝ. 104፥28፤ ራእ. 16፥10።ሙሴም እጁን ወደ ሰማያት ዘረጋ፥ በግብጽም ምድር ሁሉ ላይ ሦስት ቀን ፅኑ ጨለማ ሆነ፤ 23ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ማንም ከስፍራው አልተነሣም፤ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው። 24ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ፦ “ሂዱ፥ ጌታን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁም ከእናንተ ጋር ይሂዱ” አለው። 25ሙሴም እንዲህ አለው፦ “አንተ ደግሞ ለጌታ አምላካችን የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን በእጃችን ትሰጠናለህ። 26ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ አንድ ሰኮናም አይቀርም፥ ጌታ አምላካችንን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና፤ ጌታን የምናገለግለው በምን እንደሆነ እዚያ እስክንደርስ አናውቅም።” 27ጌታ ግን የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም። 28ፈርዖንም፦ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ተጠንቀቅ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ” አለው። 29ሙሴም፦ “እንደ ተናገረህ ይሁን፤ ፊትህን እንደገና አላይም” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 10: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ