ኦሪት ዘፀአት 13
13
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገርው፦ 2#ዘኍ. 3፥13፤ ሉቃ. 2፥23።“ማሕፀንን የሚከፈት በኩርን ሁሉ፤ በእስራኤል ልጆች መካከል፥ ከሰውም፥ ከእንስሳም ለእኔ ቀድስልኝ፥ የእኔ ነው።”
የቂጣ በዓል
3ሙሴም ሕዝቡን አለ፦ ከባርነት ቤት ከግብጽ የወጣችሁበትን ይህንን ቀን አስቡ፥ ጌታ ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ። 4እናንተ ዛሬ በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5ጌታም ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ ኬጢያውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ኤዊያውያን፥ ወደ ኢያቡሳውያንም ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር ባገባህ ጊዜ ይህችን አገልግሎት በዚህ ወር ታገለግላለህ። 6ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ለጌታ በዓል ይሆናል። 7ሰባት ቀንም ሙሉ ያልቦካ ቂጣ ትበላለህ፥ በአንተም ዘንድ እርሾ ያለበት አይታይ፥ በድንበርህም ሁሉ እርሾ አይታይ። 8በዚያም ቀን፦ “ከግብጽ በወጣሁ ጊዜ ጌታ ስላደረገልኝ ነው” ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ። 9በእጅህ እንደ ምልክት በዐይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ፥ የጌታ ሕግ በአፍህ እንዲሆን፥ ጌታ በብርቱ እጅ ከግብጽ አውጥቶሃልና። 10በተወሰነለት ጊዜ ከዓመት ወደ ዓመት ይህችን ሥርዓት ጠብቃት።
የበኩር ልጅ መቀደስ
11ጌታ ለአንተና ለአባቶችህም እንደማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር ያመጣሃል ለአንተም ይሰጥሃል፤ 12#ዘፀ. 34፥19፤20፤ ሉቃ. 2፥23።ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለጌታ ስጥ፥ የአንተ ከሆነ ከከብት ሁሉ ተባት ሆኖ አስቀድሞ የተወለደው ለጌታ ይሆናል። 13የአህያውን በኩር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ፤ የሰውንም በኩር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ። 14እንዲህም ይሆናል በሚመጣው ጊዜ ልጅህ፦ ይህ ምንድነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ፦ ጌታ በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብጽ አወጣን፤ 15ፈርዖን እንዳይለቀን ልቡን ባጸና ጊዜ ጌታ ከሰው በኩር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኩር ድረስ በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለጌታ እሠዋለሁ፥ ነገር ግን የልጆቼን በኩር ሁሉ እዋጃለሁ። 16ጌታ በብርቱ እጅ ከግብጽ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዐይኖችህም መካከል እንደ ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ።
የደመና ዓምድና የእሳት ዓምድ
17እንዲህም ሆነ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ምንም እንኳን ቅርብ ቢሆን በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር፦ “ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብጽም እንዳይመለስ” ብሏልና። 18ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ዞረው በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መንገድ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብጽ ምድር ለጦርነት ተሰልፈው ወጡ። 19#ዘፍ. 50፥25፤ ኢያ. 24፥32።ሙሴም የዮሴፍን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ “በእርግጥ እግዚአብሔር ይጎበኛችኋል፥ አጥንቶቼንም ከዚህ ከእናንተ ጋር ውሰዱት” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና። 20ከሱኮትም ወጡ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ። 21በቀንና በሌሊትም እንዲጓዙ፥ ጌታ ቀን በደመና ዓምድ መንገድ ሊመራቸው፥ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ ሊያበራላቸው ከፊታቸው ይሄድ ነበር። 22#ጥበ. 10፥17፤18፤ 18፥3።የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ አልተለየም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 13: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ