የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 16

16
መና ከሰማይ እንደ ወረደላቸው
1ከኤሊምም ተነሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር፥ በዓሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። 2የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። 3የእስራኤልም ልጆች እንዲህ አሉአቸው፦ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን ሳለን፥ ምግብ ተትረፍርፎ ስንበላ ሳለን፥ በግብጽ ምድር ሳለን በጌታ እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ ወደዚህ ምድረ በዳ አወጣችሁን።” 4#ጥበ. 16፥20-29፤ ዮሐ. 6፥31።ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከሰማይ እንጀራን ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡም ወጥተው ለቀኑ የሚበቃቸውን በቀኑ ይልቀሙ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ። 5እንዲህም ይሆናል በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ በየቀኑ ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን።” 6ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ አሉ፦ “ጌታ ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ 7በጥዋትም የጌታን ክብር ታያላችሁ፤ ምክንያቱም በጌታ ላይ ያጉረመረማችሁትን ሰምቶአልና፥ በእኛም ላይ የምታጉረመርሙ እኛ ምንድን ነን?” 8ሙሴም፦ “ጌታ በማታ የምትበሉትን ሥጋና በማለዳ ደግሞ የሚያጠግባችሁን ምግብ ሲሰጣችሁ ጌታ ያጉረመረማችሁበትን ማጉረምረም ሰምቶ ነው፤ እኛ ምንድን ነን? ማጉረምረማችሁ በጌታ ላይ ነው እንጂ በእኛ ላይ አይደለም” አለ። 9ሙሴም አሮንን፦ “ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ‘ማጉረምረማችሁን ሰምቶአልና ወደ ጌታ ፊት ቅረቡ በላቸው’” አለው። 10እንዲህም ሆነ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አዞሩ፤ እነሆም የጌታ ክብር በደመናው ታየ። 11ጌታም ሙሴን አለው፦ 12የእስራኤልን ልጆች ማጉረምረማቸውን ሰማሁ፦ እንዲህ በላቸው “ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”
13እንዲህም ሆነ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ሸፈኑት ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ነበር። 14ጤዛውም ከተነነ በኋላ፥ በመሬት ላይ ስስ የሆነ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ መሬት ላይ ታየ። 15#1ቆሮ. 10፥3።የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደሆነ አላወቁምና ሁሉም ሰው ወንድሙን፦ “ይህ ምንድነው?” በማለት ተጠያየቁ። ሙሴም፦ “እንድትበሉት ጌታ የሰጣችሁ ምግብ ነው።” 16ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ “እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ዖሜር#16፥16 መስፈሪያ፤ ከሁለት ሊትር ትንሽ ከፍ የሚል። ይውሰድ።” 17የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዳንዶቹ ብዙ አንዳንዶቹ ጥቂት ሰበሰቡ። 18#2ቆሮ. 8፥15።በዖሜርም በሰፈሩት ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አላነሰውም፤ የሰበሰቡት እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ነው። 19ሙሴም፦ “ማንም ሰው እስከ ጥዋት ከእርሱ ምንም እንዳያስቀር” አላቸው። 20ሙሴንም አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ጥቂት እስከ ጥዋት አስቀሩ፥ እርሱም በስብሶ ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቆጣቸው።
21ጥዋት ጥዋት እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሐይም በሞቀ ጊዜ ቀለጠ። 22እንዲህም ሆነ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው ሁለት ዖሜር ምግብ ለአንድ ሰው ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም መሪዎች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት። 23#ዘፀ. 20፥8-11።እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ የተናገረው ይህ ነው፦ ነገ የዕረፍት ሰንበት ነው፥ ለጌታ የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ተውት ለጥዋት ለእናንተ አስቀምጡት።” 24ሙሴም እንዳዘዘ ለጥዋት አስቀመጡት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልነበረበትም። 25ሙሴም፦ “ዛሬ ብሉት፥ ዛሬ ለጌታ ሰንበት ነውና፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም። 26ስድስት ቀን ትሰበስባላችሁ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይኖርም።” 27በሰባተኛውም ቀን ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊሰበስቡ ወጡ፥ ምንም አላገኙም። 28ጌታም ሙሴን አለው፦ “ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እምቢ የምትሉት እስከ መቼ ነው? 29ጌታ ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን ምግብ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፤ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይውጣ።” 30ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።
31 # ዘኍ. 11፥7፤8። የእስራኤልም ቤት ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ፍሬ ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው። 32ሙሴም፦ “ጌታ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን ምግብ እንዲያዩ ከእርሱ አንድ ዖሜር ሙሉ በትውልዳችሁ ሁሉ ይጠበቅ” አለ። 33#ዕብ. 9፥4።ሙሴም አሮንን አለው፦ “አንድ ማድጋ ወስደህ ዖሜር ሙሉ መና አኑርበት፥ በትውልዳችሁም ተጠበቆ እንዲኖር በጌታ ፊት አስቀምጠው።” 34ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ተጠብቆ እንዲኖር አሮን በምስክሩ ፊት አስቀምጠው። 35#ኢያ. 5፥12።የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ። 36ዖሜርም የኢፍ አንድ አሥረኛ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ