ኦሪት ዘፀአት 18
18
የይትሮ ምክር
1የምድያን ካህን የሙሴ አማት ይትሮ እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ ጌታም እስራኤልን ከግብጽ እንዳወጣ ሰማ። 2#ዘፀ. 2፥21፤22።የሙሴ አማት ይትሮ መልሷት የነበረችውን የሙሴን ሚስት ጺፖራን ወሰደ። 3#የሐዋ. 7፥29።እንዲሁም ሁለቱን ልጆቿን ጭምር። የአንደኛው ስም ጌርሾም ነበረ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ብሏልና፤ 4የሁለተኛውም ስም ኤሊዔዘር ነበረ፦ “የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ” ብሏልና። 5የሙሴ አማት ይትሮ፥ ከልጆቹና ሚስቱ ጋር በምድረ በዳ ሰፍሮ ወደ ነበረበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ሙሴ መጣ። 6ሙሴንም፦ “እኔ አማትህ ይትሮ፥ ሚስትህና ከእርሷም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ ወደ አንተ መጥተናል” አለው። 7ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ። 8ሙሴም ጌታ በፈርዖንና በግብጽ ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ ጌታም እንዳዳናቸው ለአማቱ ተረከለት። 9ይትሮም ጌታ ለእስራኤል ስላደረገው መልካም ነገር ሁሉ፥ ከግብጽም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው። 10ይትሮም እንዲህ አለ፦ “ከግብጽ እጅና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብጽም እጅ በታች ሕዝቡን ያዳነ ጌታ ይባረክ። 11በትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር ላይ ጌታ ከአማልክት ሁሉ እንደሚበልጥ አሁን አወቅሁ።” 12የሙሴ አማት ይትሮም የሚቃጠል ቊርባንና መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ አሮንና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሊመገቡ ከሙሴ አማት ጋር መጡ።
13በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። 14የሙሴ አማትም ለሕዝቡ ያደርግ የነበረውን ሁሉ ባየ ጊዜ፦ “ለሕዝቡ የምታደርገው ይሄ ነገር ምንድነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመዋል፥ አንተ ብቻህን ለምን ተቀምጠሃል?” አለው። 15ሙሴም አማቱን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ 16ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በአንድ ሰውና በጎረቤቱ መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ።” 17የሙሴ አማትም አለው፦ “እያደረግህ ያለኸው ነገር መልካም አይደለም። 18አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ ይህ ነገር ይከብድሃልና፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። 19አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቡን አቅርብ፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አቅርብ፤ 20ሥርዓቱንና ሕጉን አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድና የሚያደርጉትን ሥራ አሳውቃቸው። 21አንተም ከሕዝቡ ሁሉ መስራት የሚችሉ፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፥ የታመኑ፥ የጉቦ ትርፍን የሚጠሉ ሰዎችን ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የዐሥር አለቆችን ሹምላቸው። 22በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ ትልቁን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ትንሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልሃል። 23ይህንም ብታደርግና፥ እግዚአብሔር ቢያዝዝህ፥ መቋቋም ትችላለህ፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው በሰላም ይሄዳል።” 24ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ። 25ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ መስራት የሚችሉ ሰዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የአምሳ አለቆች፥ የዐሥር አለቆች አድርጎ ሾማቸው። 26በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበዳቸውን ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ትንሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። 27ሙሴም አማቱን ሸኘው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 18: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ