የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 16

16
እምነተ ቢስ የእግዚአብሔር ሙሽራ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኩሰትዋን አስታውቃት፥ 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፦ መሠረትሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፥ አባትሽ አሞራዊ ነበረ፥ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። 4ስትወለጂ፥ በተወለድሽበት በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቆረጠም ነበር፥ ንጹሕም እንድትሆኚ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨው አልታሸሽም፥ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። 5አዝኖልሽ ከእነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ሊያደርግልሽ አንድም ዐይን አልራራልሽም፥ ነገር ግን በተወለድሽበት ቀን ሰውነትሽ የተጠላ ስለ ነበር በሜዳ ላይ ተጣልሽ።
6በአንቺም በኩል አለፍሁ፥ በደምሽም ውስጥ ስትንፈራገጪ አየሁሽ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፥ አዎን በደምሽ ውስጥ እያለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ። 7በሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በጌጦች አጌጥሽ፥ ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፥ ጠጉርሽም አደገ፥ ሆኖም ዕርቃንሽንና ራቁትሽን ነበርሽ። 8በአንቺ በኩል አለፍሁ፥ አየሁሽም፥ እነሆ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበር፥ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ላይ ዘረጋሁና ዕርቃንሽን ሸፈንሁ፥ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም የእኔ ሆንሽ። 9በውኃ አጠብሁሽ፥ ደምሽን ከላይሽ ላይ አጠራሁ፥ በዘይትም ቀባሁሽ። 10ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ፥ ከጥሩ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፥ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ፥ ውድ መደረቢያም ደረብሁልሽ። 11በጌጥ አስጌጥሁሽ፥ በእጅሽ ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ሐብል አደረግሁልሽ። 12በአፍንጫሽ ቀለበት፥ በጆሮሽ ጉትቻ፥ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁ። 13በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታ፥ ሐርና ወርቀዘቦ ነበር፥ የላመ ዱቄት፥ ማርና ዘይትም በላሽ፥ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ፥ ለንግሥትነትም በቃሽ። 14በአንቺ ላይ ካኖርኋት ከውበቴ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ስምሽ በሕዝቦች መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15ነገር ግን በውበትሽ ተመክተሻል፥ በስምሽም አመንዝረሻል ምንዝርናሽንም ከአላፊ አግዳሚው ሁሉ ጋር አበዛሽ። 16ከልብሶችሽ ጥቂቱን ወስደሽ የመስገጃ ስፍራዎችሽ ላይ በዝንጉርጉር ልብስ ያስጌጥሻቸውን መስገጆች ለራስሽ ሠራሽ በዚያም ገለሞትሽ፥ እንዲህም ያለ ነገር ከአሁን በፊት አልነበረም፥ ከእንግዲህም ወዲያ አይሆንም። 17የሰጠሁሽን ከወርቄና ከብሬ የተሠራውን የሚያምር ጌጣጌጥ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ ሠራሽ፥ ከእነርሱም ጋር አመነዘርሽ። 18ወርቀዘቦ ልብሶችሽንም ወስደሽ አለበስሻቸው፥ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አስቀመጥሽ። 19የሰጠሁሽን ምግቤን፥ እንድትበይው የሰጠሁሽን ምርጥ ዱቄት፥ ዘይትና ማር ጣፋጭ ሽታ አድርገሽ በፊታቸው አስቀመጥሽ፥ እንዲህም ተደርጓል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20ለእኔ የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወስደሽ ለእነርሱ መብል እንዲሆኑ ሠዋሻቸው። አመንዝራነትሽ አንሶ ነውን? 21ልጆቼን አረድሽ፥ በእነርሱም በኩል ስታልፊ ለእነርሱ ሰጠሻቸው፤ 22በርኩሰቶችሽ ሁሉና በአመንዝራነትሽ ዕርቃንሽን ሆነሽ ተራቁተሽም በደምሽ ውስጥ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት የልጅነትሽን ጊዜ አላስታወስሺም።
23ከዚህ ሁሉ ክፋትሽ በኋላ ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ 24ለራስሽ ጉብታን ሠራሽ፥ በየአደባባዩም ከፍ ያለ ቦታን ለራስሽ አዘጋጀሽ። 25በየመንገዱ ራስ ሁሉ ላይ ከፍ ያለውን ቦታሽን ሠራሽ፥ ውበትሽንም አረከስሽ፥ ለአላፊ አግዳሚው ሁሉ እግርሽን ከፈትሽ፥ አመንዝራነትሽንም አበዛሽ። 26በሥጋ ከደለቡ ግብጻውያን ጐረቤቶችሽ ጋር አመነዘርሽ፥ እኔንም ለማስቆጣት አመንዝራነትሽን አበዛሽ። 27እነሆ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቻለሁ፥ ድርሻሽንም ቀንሻለሁ፥ ከክፉ መንገድሽ የተነሣ ለሚያፍሩ፥ ለጠላቶችሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች ፈቃድ አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ። 28አልረካሽምና ከአሦራውያን ልጆች ጋር አመነዘርሽ፥ ከእነርሱም ጋር አመነዘርሽ አሁንም አልረካሽም። 29በከነዓን ምድር ከከላውዴዎን ጋር አመንዝራነትሽን አበዛሽ። በዚህም አልረካሽም።
30የማታፍር አመንዝራ ሴት ሥራ፥ እነዚህን ሁሉ ስትሠሪ ልብሽ ምንኛ ደካማ ነው? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31በየመንገዱ ራስ የምንዝርናሽን ስፍራ ሠርተሻል በየአደባባዩም ከፍ ያለውን ቦታሽን አድርገሻል። ዋጋዋን እንደምትንቅ እንደ ጋለሞታ አልሆንሽም። 32በባሏ ፋንታ ሌሎችን የምታስተናግድ አመንዝራ ሴት ሆነሻል። 33ለአመንዝራዎች ሁሉ ሥጦታ ይሰጡአቸዋል፥ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ሥጦታሽን ትሰጫለሽ፥ ለአመንዝራነትሽ ከየአቅጣጫው ወደ አንቺ እንዲገቡ ጉቦ ትሰጫቸዋለሽ። 34አመንዝራነትሽ ከሌሎች ሴቶች የተለየ ነው፥ ማንም ለዝሙት የሚከተልሽ የለም፤ ማንም ዋጋ ሳይሰጥሽ አንቺ ዋጋ ትሰጫለሽ፤ የተለየሽም ሆንሽ።
35ስለዚህ አመንዝራ ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሚ። 36ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍትወትሽ ስለ ፈሰሰ፥ ከወዳጆችሽ ጋር ባደረግሽው ዝሙት ዕርቃንሽ ስለ ተገለጠ፥ ስለ ርኩሰትሽም ጣዖታት ሁሉና ለእነርሱ ስለ ሰጠሻቸው ልጆች ደም፥ 37ስለዚህ እነሆ እኔ ደስ የተሰኘሽባቸውን ወዳጆችሽን ሁሉ፥ የወደድሻቸውን ሁሉ ከጠላሻቸው ሁሉ ጋር እሰበስባቸዋለሁ፤ ሁሉንም ከየአቅጣጫው በአንቺ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፥ ራቁትነትሽን ሁሉ እንዲያዩ በፊታቸው ዕርቃንሽን እገልጣለሁ። 38በአመንዝሮችና በደም አፍሳሽ ሴቶች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፥ የመዓትንና የቅንዓትን ደም አመጣብሻለሁ። 39በእጃቸውም አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ ጉብታሽን ያፈርሳሉ፥ ከፍ ያለውንም ቦታሽን ይገለብጣሉ፤ ልብሶችሽንም ይገፉሻል፥ የሚያምሩ ጌጣጌጦችሽን ይወስዳሉ፥ ዕርቃንሽንና ዕራቁትሽን ይተዉሻል። 40የሚረብሽ ሕዝብ በአንቺ ላይ ያመጡብሻል፥ በድንጋይም ይወግሩሻል፥ በሰይፋቸውም ይቆራርጡሻል። 41ቤቶችሽን በእሳት ያቃጥላሉ፥ በብዙ ሴቶችም ፊት በላይሽ ፍርድን ያደርጉብሻል፥ አመንዝራነትሽን አስተውሻለሁ፥ ከእንግዲህም በኋላ ዋጋ አትሰጪም። 42በአንቺ ላይ ያለውን መዓቴን አቆማለሁ፥ ቅንዓቴም ከአንቺ ይርቃል፥ እኔም ዝም እላለሁ፥ ከእንግዲህም አልቆጣም። 43በእነዚህ ነገሮች ሁሉ አስቆጣሽኝ እንጂ የልጅነትሽን ወራት አላስታወስሺም፤ ስለዚህ እነሆ እኔ ደግሞ መንገድሽን በራስሽ ላይ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በርኩሰቶችሽ ሁሉ ላይ ሌላ ነውር አትጨምሪም።
44እነሆ በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፦ “ሴት ልጇ እንደ እናቷ ናት” እያለ ምሳሌ ይመስልብሻል። 45አንቺ ባሏንና ልጆችዋን የጠላች የእናትሽ ልጅ ነሽ፥ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የጠሉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ፥ እናታችሁ ኬጢያዊት ነበረች አባታችሁም አሞራዊ ነበረ። 46ታላቅ እኅትሽ ከሴቶች ልጆችዋ ጋር ከአንቺ በስተ ሰሜን የምትቀመጥ ሰማርያ ናት፥ ታናሽ እኅትሽም ከሴቶች ልጆችዋ ጋር ከአንቺ በስተ ደቡብ የምትቀመጥ ሰዶም ናት። 47አንቺ በእነርሱ መንገድ መሄድሽና ርኩሰታቸውንም መከተልሽ ብቻ ሳይሆን፥ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመንገድሽ ሁሉ ከእነርሱ የበለጠ ምግባረ ብልሹ ነበርሽ። 48እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴቶች ልጆችሽ እንዳደረጋችሁት ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ አላደረጉም። 49እነሆ፥ የእኅትሽ የሰዶም በደል ይህ ነበር፤ በእርሷና በሴቶች ልጆቿ ትዕቢት፥ የምግብ ጥጋብ፥ የበለጸገ ምቾት ነበረ፥ የችግረኛውንና የድሀውንም እጅ አላጸናችም። 50ትዕቢተኞች ነበሩ፥ በፊቴም ርኩስ ነገር አደረጉ፥ ስለዚህ ባየሁት ጊዜ አስወገድኋቸው። 51ሰማርያ የኃጢአትሽን ግማሽ አልሠራችም፤ አንቺ ግን ከእነርሱ ይልቅ ርኩሰትሽን አበዛሽ፥ በሥራሽም ርኩሰት ሁሉ እኅቶችሽን ጻድቃን አስመሰልሻቸው። 52አንቺም ደግሞ ለእኅቶችሽ ስለ ፈረድሽ እፍረትሽን ተሸከሚ፥ ከእነርሱ የባሰ ኃጢአት ሠርተሻልና ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ናቸው፥ እኅቶችሽንም ስለ አጸደቅሻቸው እፈሪ እፍረትሽንም ተሸከሚ። 53ምርኮአቸውን እመልሳለሁ፤ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ በመካከላቸው ያለውን የአንቺንም ምርኮ እመልሳለሁ፥ 54ለእነርሱ መጽናናት ስለሆንሻቸው እፍረትን እንድትሸከሚና በሠራሽውም ሁሉ እንድታፍሪ ነው። 55እኅቶችሽ ሰዶምና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ ሰማርያና ሴቶች ልጆችዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ፥ አንቺና ሴቶች ልጆችሽም ወደ ቀድሞ ሁኔታችሁ ትመለሳላችሁ። 56በትዕቢትሽ ቀን እኅትሽ ሰዶም በአፍሽ መተረቻ አልነበረችምን? 57ክፋትሽ ሳይገለጥ በፊት፤ አሁን ለአራም#16፥57 አንዳንድ ትርጉሞች ኤዶም ይላሉ፥ አንዳንዶቹ ደግሞ ሶርያ ይላሉ። ሴቶች ልጆችና ለጎረቤቶችዋ ሁሉ፥ በዙሪያሽም ላሉት ለሚንቁሽ ለፍልስጥኤም ሴቶች ልጆች እንደ እርሷ መሰደቢያ ሆነሻል። 58ክፋትሽንና ርኩሰነትሽን መሸከም አለብሽ፥ ይላል ጌታ።
ለዘለዓለም የሚጸና ቃል ኪዳን
59ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ቃል ኪዳንን በማፍረስ መሐላን ንቀሻልና፥ አንቺ እንዳደረግሽ እኔ ደግሞ አደርግብሻለሁ። 60ነገር ግን በልጅነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር የመሠረትኩትን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ፥ የዘለዓለምንም ቃል ኪዳን አቆማለሁ። 61የአንቺ ታላቅና የአንቺ ታናሽ እኅቶችሽን በተቀበልሽ ጊዜ መንገድሽን ታስቢያለሽ ታፍሪያለሽም፥ ሴቶች ልጆች እንዲሆኑሽም ለአንቺ እሰጣቸዋለሁ፥ ከቃል ኪዳንሽ የተነሣ ግን አይደለም። 62ቃል ኪዳኔን ከአንቺ ጋር አቆማለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቂያለሽ፤ 63ያደረግሽውን ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፥ እንድታስቢውና እንድታፍሪ፥ ከውርደትሽም የተነሣ ደግሞ አፍሽን እንዳትከፍቺ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ