የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 23

23
ኦሆላ እና ኦሆሊባ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንድ እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። 3በግብጽ አመነዘሩ፤ በወጣትነታቸው አመነዘሩ፤ በዚያ ጡቶቻቸው ተዳሰሱ፥ በዚያም የድንግልናቸው የጡቶች ጫፍ ተዳበሱ። 4ስማቸውም፦ የታላቂቱ ኦሆላ የእኅትዋም ኦሆሊባ ነበረ። የእኔም ሆኑ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም፦ ኦሆላ ሰማርያ ናት፥ ኦሆሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።
5ኦሖላም የእኔ ሆና ሳለ አመነዘረች፥ ጦረኞች ከሆኑት አሦራውያን ውሽሞችዋ ጋር በፍትወት ተከተለቻቸው። 6እነርሱም ሰማያዊ የለበሱ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶች፥ ፈረስ የሚጋልቡ ፈረሰኞች ነበሩ። 7ዝሙቷንም ከተመረጡ የአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፥ በፍትወት ከተከተለቻቸው ከጣዖቶቻቸው ሁሉ ጋር እራስዋን አረከሰች። 8ከግብጽ ጀምሮ የነበረውን አመንዝራነቷን አልተወችም፤ በወጣትነትዋ ጊዜ ወንዶች ከእርሷ ጋር ተኝተው ነበርና፥ የድንግልናዋንም የጡቶቿ ጫፎች ዳብሰው ነበርና፥ ፍትወታቸውንም አፍስሰውባት ነበርና። 9ስለዚህ በፍትወት በተከተለቻቸው በውሽሞችዋ እጅ፥ በአሦር ልጆች እጅ አሳልፌ ሰጠኋት። 10እነርሱም ዕራቁትነትዋን ገለጡ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ወሰዱ፤ እርሷንም በሰይፍ ገደሉ፤ በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች፥ ፍርድም ተፈጸመባት።
11እኅትዋ ኦሆሊባ ይህን አየች፥ ሆኖም በፍትወቷና በአመንዝራነቷ ከእርሷ ይልቅ ብልሹ ነበረች፥ ይህም ከእኅትዋ ይልቅ የበዛ ነበር። 12አሦራውያንን፥ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች፥ ጌጠኛ ልብስ የለበሱ ጦረኞች፥ በፈረሶችን የሚጋልቡ ፈረሰኞች፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶችን በፍትወት ተከተለቻቸው። 13እራስዋን እንዳረከሰች አየሁ፤ ሁለቱም በአንድ መንገድ ሄዱ። 14አመንዝራነቷን ቀጠለችበት፤ በቀይ ቀለም የተሳለ የከለዳውያን ስዕል፥ በግድግዳ ላይ የተቀረጸ የወንዶች ምስል አየች። 15በወገባቸው ዝናር የታጠቁ፥ በራሳቸውም ላይ መጠምጠሚያ ያንጠለጠሉ፥ ሁሉም የተወለዱባት አገር የከለዳ የሆነች የባቢሎን ልጆች የሆኑትን ባለሥልጣኖችን ይመስሉ ነበር። 16በዓይኗም ባየቻቸው ጊዜ በፍትወት ተከተለቻቸው፥ ወደ ከላውዴዎን ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች። 17የባቢሎንም ልጆች ወደ እርሷ፥ ወደ ፍቅር አልጋ ገቡ፥ በዝሙታቸውም አረከሱአት፤ እርሷም በእነርሱ ረከሰች ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች። 18ዝሙቷን ገለጠች፥ ዕርቃንዋንም ገለጠች፥ ነፍሴ ከእኅትዋ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርሷም ተለየች። 19ሆኖም በግብጽ ምድር ያመነዘረችበትን የወጣትነትዋን ዘመን አስባ ዝሙቷን አበዛች። 20ሥጋቸው እንደ አህዮች ሥጋ፥ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን ምልምሎች በፍትወት ተከተለቻቸው። 21ስለ ወጣትነት ጡቶችሽን ግብጻውያን ጡቶችሽን የዳበሱበትን ጊዜ የወጣትነትሽን ሴሰኝነት አሰብሽ።
22ስለዚህ ኦሆሊባ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየቻቸው ወዳጆችሽን አስነሣብሻለሁ፥ እነርሱንም ከየአቅጣጫው በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። 23እነርሱም የባቢሎን ልጆች፥ ከለዳውያን ሁሉ ፋቁድ፥ ሾዓ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር የአሦር ልጆች ሁሉ፥ ሁሉም መልከ መልካም ወጣቶች፥ ገዢዎች፥ ባለ ሥልጣናት፥ መኰንኖችና የተጠሩ፥ ሁሉም ፈረስ የሚጋልቡ ናቸው። 24መሣሪያ፥ ሠረገላና መንኰራኵር ይዘው፥ ብዙ ሕዝብ ሆነው በአንቺ ላይ ይመጣሉ፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ ራስ ቁርም ይዘው በዙሪያሽ ይዘጋጁብሻል፥ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፥ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል። 25በቁጣ እንዲቀርቡሽ ቅናቴን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ፥ አፍንጫሽንና ጆሮሽን ይቆርጣሉ፤ ቀሪሽም በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችሽን ይወስዳሉ፥ ከአንቺም የቀረው በእሳት ይበላል። 26ልብስሽን ይገፍፉሻል የሚያማምሩ ጌጣጌጦችሽን ይወስዳሉ። 27ሴሰኝነትሽንና ከግብጽ ምድር ያመጣሽውን ዝሙትሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፥ ዓይንሽን ወደ እነርሱ አታነሺም፥ ግብጽንም ዳግም አታስቢም። 28ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽም በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ 29እነርሱም በጥል ይቀርቡሻል፥ የድካምሽን ፍሬ ሁሉ ይወስዳሉ፥ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፥ የዝሙትሽ ዕራቁትነት፥ ሴሰኝነትሽና ግልሙትናሽ ይገለጣል። 30ከአገሮች ጋር ስላመነዘርሽ በጣዖቶቻቸውም ስለ ረከስሽ ይህን አደረጉብሽ። 31በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ የእርሷን ጽዋ በእጅሽ እሰጥሻለሁ። 32ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥልቅና ሰፊ የሆነውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ ብዙም ስለሚይዝ መሳቂያና መሳለቂያም ትሆኛለሽ። 33የድንጋጤና የጥፋት ጽዋ በሆነው በእኅትሽ በሰማሪያ ጽዋ፥ በስካርና በኀዘን ትሞዪአለሽ። 34ትጠጪዋለሽ፥ ትጨልጪዋለሽም፥ ገሉን#23፥34 የሸክላ ስባሪ ታኝኪዋለሽ፥ ጡትሽንም ትቆራርጪአለሽ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 35ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለረሳሽኝ፥ ወደ ኋላሽም ስለጣልሽኝ፥ አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽን ተሸከሚ።
36ጌታ እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በኦሆላና በኦሆሊባ ትፈርዳለህን? ርኩሰታቸውን ንገራቸው። 37አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፤ ከጣዖቶቻቸው ጋር አመንዝረዋል፤ ለእኔ የወለዷቸውን ልጆቻቸውን እንኳ መብል እንዲሆኑ አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። 38ደግሞም ይህን አደረጉብኝ፦ በዚያኑ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል፥ ሰንበቶቼንም ሽረዋል። 39ልጆቻቸውን ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ፥ በዚያው ቀን ሊያረክሱት ወደ መቅደሴ ገብተዋልና፤ እነሆም በቤቴ ውስጥ ይህን አደረጉ። 40ደግሞም መልእክተኛ ወደ ተላከባቸው፥ ከሩቅም ወደሚመጡ ሰዎች ልከዋል፥ እነሆም መጡ፤ ታጠብሽላቸው ዓይንሽን ተኳልሽ፥ ጌጥም አደረግሽ፤ 41ክብር ባለው አልጋ ላይ ተቀመጥሽ፥ በፊት ለፊቱም ማዕድ ተዘጋጅቶ ነበር፥ ዕጣኔንና ዘይቴንም በዚያ ላይ አስቀመጥሽ። 42የደስተኞችም ድምፅ በእርሷ ዘንድ ነበረ፥ ከብዙም ሰዎች ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረበዳ መጡ፥ በእጃቸው አንበር በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ። 43እኔም በዝሙት ላረጀችው፦ አሁን ከእርሷ ጋር ያመነዝራሉ፥ እርሷም ታመነዝራለች አልሁ። 44ሰው ወደ አመንዝራ እንደሚገባ ወደ እርሷ ገቡ፤ ስለዚህ አመንዝራ ወደ ሆኑት ወደ ኦሆላና ወደ ኦሆሊባ ገቡ። 45ጻጽቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል፤ ምክንያቱም አመንዝሮች ናቸውና፥ ደምም በእጃቸው አለና።
46ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፥ ለፍርሃትና ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 47ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል፥ በሰይፋቸው ይቆርጡአቸዋል፤ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን ይገድላሉ፥ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። 48ሴቶችም ሁሉ እንደ አመንዝራነታችሁ እንዳይሠሩ፥ እንዲጠነቀቁ አመንዝራነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ። 49አመንዝራነታችሁን በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ#23፥49 የአመንዝራነታችሁን ዋጋ ታገኛላችሁ፥ የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፥ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ