የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 26

26
በጢሮስ ላይ የተነገረ አዋጅ
1 # ኢሳ. 23፥1-18፤ ኢዮብ 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9፤10፤ ዘካ. 9፥1-4፤ ማቴ. 11፥21፤22፤ ሉቃ. 10፥13፤14። እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ ጢሮስ በኢየሩሳሌም ላይ፦ “እሰይ የሕዝቦች በር የነበረች ተሰበረች፤ ወደ እኔም ተመለሰች፤ እርሷ ስለፈረሰች እኔ እሞላለሁ፤” ብላለችና። 3ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ! እነሆ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፥ ባሕር ሞገድን እንደሚያስነሣ እንዲሁ ብዙ ሕዝቦችን አስነሣብሻለሁ። 4የጢሮስን ቅጥሮች ያፈርሳሉ፥ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ አፈሯን ከእርሷ ላይ ጠርጌ የተራቆተ ዓለት አደርጋታለሁ። 5በባሕር ውስጥ የመረብ ማስጫ ትሆናለች፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ፤ ለሕዝቦችም ብዝበዛ ትሆናለች። 6በሜዳ ያሉት ሴቶች ልጆችዋም በሰይፍ ይገደላሉ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
7ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ ከሰሜን የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነዖርን ከፈረሶች፥ ከሰረገሎች፥ ከፈረሰኞች፥ ከጉባኤና ከብዙ ሕዝብ ጋር በጢሮስ ላይ አመጣለሁ። 8በሜዳ ያሉትን ሴቶችን ልጆችሽን በሰይፍ ይገድላቸዋል፤ በአንቺ ላይ ምሽግ ይሠራል፥ ደለልም በአንቺ ላይ ይደለድላል፥ በአንቺም ላይ ጋሻ ያነሣል። 9ግንብ ማፍረሻውን በቅጥርሽ ላይ ያነጣጥራል፥ ግንብሽንም በሰይፉ ያፈርሳል። 10ከፈረሶቹ ብዛት የተነሣ አቧራቸው ይሸፍንሻል፤ ሰዎች ወደ ፈረስች ከተማ እንደሚገቡ እርሱ በበሮችሽ በሚገባበት ጊዜ፥ ከፈረሰኞች፥ ከመንኩራኩሮች እና ከሰረገሎች ድምፅ የተነሣ ቅጥሮችሽ ይናወጣሉ። 11በፈረሶቹ ኮቴዎች ጎዳናዎችሽን ሁሉ ይረጋግጣል፥ ሕዝብሽንም በሰይፍ ይገድላል፥ የብርታትሽ ምሰሶዎች ወደ መሬት ይወድቃሉ። 12ሀብትሽን ይዘርፋሉ፥ ሸቀጣ ሸቀጥሽንም ይበዘብዛሉ፤ ቅጥርሽን ያፈርሳሉ፥ የተዋቡ ቤቶችሽን ያጠፋሉ፤ ድንጋይሽን፥ እንጨትሽንና አፈርሽን በውኆች መካከል ያስቀምጣሉ። 13#ራእ. 18፥22።የዘፈንሽን ብዛት#26፥13 አንዳንድ ትርጉሞች “ድምፅ” ይላሉ ዕብራይስጡ ግን ብዛት ይለዋል። አስቆማለሁ፤ የበገናሽ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም። 14የተራቆተ ዓለት አደርግሻለሁ፤ የመረብ ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ዳግምም አትሠሪም፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
15ጌታ እግዚአብሔር ጢሮስን እንዲህ ይላታል፦ የቆሰሉት ባቃሰቱ ጊዜ፥ በውስጥሽ እልቂት በሆነ ጊዜ፥ ከውድቀትሽ ድምፅ የተነሣ ደሴቶች አይነዋወጡምን? 16#ራእ. 18፥9፤10።በዚያን ጊዜ የባሕር አለቆች ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውን ያስቀምጣሉ፥ ወርቀዘቦ ልብሳቸውንም ያወልቃሉ፤ መንቀጥቀጥን ይለብሳሉ፥ በመሬት ላይ ይቀመጣሉ፥ ሁልጊዜም ይንቀጠቀጣሉ፥ በአንቺም#26፥16 በአንቺ ላይ በደረሰው ነገር ይደነቃሉ። 17በአንቺ ላይ ሙሾ ያወርዳሉ፥ እንዲህም ይሉሻል፦ ከባሕር የተቀመጥሽ በባሕርም ውስጥ የጸናሽ፥ ከሚቀመጡብሽም ጋር በዙሪያሽ የሚኖሩትን ሁሉ ያስፈራሽ፥ ዝነኛ ከተማ ሆይ፥ እንዴት ጠፋሽ! 18አሁን በውድቀትሽ ቀን ደሴቶች ይንቀጠቀጣሉ፥ በባሕር ያሉ ደሴቶችም ከመጥፋትሽ#26፥18 ዕብራይስጡ ከመውጣትሽ የተነሣ ይላል። የተነሣ ይደነግጣሉ።
19ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰው እንደማይኖርባቸው ከተሞች ባድማ ከተማ ባደረግሁሽ ጊዜ፥ ጥልቁንም በላይሽ ላይ ባመጣሁብሽ ጊዜ፥ ብዙ ውኆችም ይከድኑሻል፥ 20የጥንት ሕዝብ ወዳሉበት ጉድጓድ ከሚወርዱት ጋር አወርድሻለሁ፥ የሚኖርብሽም እንዳይገኝ ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ቀድሞ በፈረሰችው ስፍራ፥ በታችኛይቱ ምድር አኖርሻለሁ፤ ጌጥሽንም በሕያዋን ምድር አላኖርም። 21#ራእ. 18፥21።ለድንጋጤ አደርግሻለሁ፥ እንግዲህም አትኖሪም፤ ትፈለጊአለሽ ለዘለዓለምም አትገኚም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ