የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 30

30
ለግብጽ የወጣ ሙሾ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አልቅሱ፥ ለቀኑ ወዮ! 3ቀኑ ቅርብ ነውና፥ የጌታ ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የሕዝቦች ጊዜ ይሆናል። 4በግብጽ ላይ ሰይፍ ይመጣል፥ የተገደሉት በግብጽ ውስጥ ሲወድቁ፥ በኢትዮጵያ ጭንቀት ይሆናል፤ ብዛትዋን ይወስዳሉ፥ መሠረቶቿንም ያፈርሳሉ። 5ኢትዮጵያ፥ ፉጥ፥ ሉድ፥ ባዕዳን ሁሉ፥ ኩብና የቃል ኪዳኑ ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
6ጌታ እንዲህ ይላል፦ ግብጽን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴቬኔ ድረስ በእርሷ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 7ባድማ በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ። 8እሳትን በግብጽ ሳነድድ፥ ረዳቶችዋም ሁሉ ሲሰበሩ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 9በዚያ ቀን ያለ ስጋት የተቀመጠችውን ኢትዮጵያን ለማስፈራራት መልእክተኞች ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብጽም ቀን ጭንቀት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ መጥቷልና።
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብጽን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አጠፋዋለሁ። 11እርሱና ከሕዝቦች ሁሉ ርህራሄ የሌላቸው ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብጽ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በሬሳ ይሞላሉ። 12ወንዞችን አደርቃለሁ፥ ምድሪቱን በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሞላዋን በባዕዳን እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ።
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶችን አስወግዳለሁ፥ ምስሎችንም ከኖፍ#30፥13 አንዳንድ ትርጉሞች ሜምፎስ ይላሉ። አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከግብጽ ምድር ገዢ አይነሳም፥ በግብጽ ምድር ላይ ፍርሃትን አኖራለሁ። 14ጳትሮስን ባድማ አደርጋለሁ፥ በጾዓን እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖ ላይም ፍርድን አመጣለሁ። 15የግብጽ ምሽግ በሆነችው በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፤ የኖን ብዛት አጠፋለሁ። 16በግብጽ እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲን ትጨነቃለች፥ ኖ ትሰባበራለች፥ ኖፍ በቀን ጠላቶች ያጠቁአታል። 17የአቬንና የፊ-ቤሴት ወጣቶች በሰይፍ ይወድቃሉ፥ እነዚህም ተማርከው ይወሰዳሉ። 18በዚያ የግብጽን ቀንበር በምሰብርበት ጊዜ፥ በትሐፍንሔስ ቀኑ ይጨልማል፥ የኃይልዋ ትዕቢት በውስጧ ይጠፋል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ተማርከው ይወሰዳሉ። 19እንግዲህ በግብጽ ላይ ፍርድን አመጣለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
በፈርዖን ላይ የተነገረ አዋጅ
20እንዲህም ሆነ በዓሥራ አንደኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በሰባተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብጽን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፤ እነሆ እንዲድን በጨርቅ አልተጠቀለለም፥ ሰይፉን ለመያዝ እንዲጠነክር አልታሰረም። 22ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የበረታችውንና የተሰበረችውን ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ እጥለዋለሁ። 23ግብጻውያንን ወደ ሕዝቦች እበትናለሁ፥ ወደ ሁሉም አገሮች እዘራቸዋለሁ። 24የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ አኖራለሁ፤ የፈርዖንንም ክንድ እሰብራለሁ፥ እሱም በፊቱ ክፉኛ እንደቆሰለ ሰው ያቃስታል። 25የባቢሎንን ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፥ የፈርዖን ክንድ ግን ይዝላል፤ ሰይፌን በባቢሎን ንጉሥ እጅ በአኖርሁ ጊዜ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 26ግብጻውያንን ወደ ሕዝቦች እበትናለሁ፥ ወደ ሁሉም አገሮች እዘራቸዋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ