ትንቢተ ሕዝቅኤል 33
33
ሕዝቅኤል የእስራኤል ዘብ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ለሕዝብህ ልጆች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ ሰይፍን በምድር ላይ ባመጣሁ ጊዜ፥ የምድሪቱ ሕዝብ ከመካከላቸው አንድ ሰው ወስደው ለራሳቸው ዘበኛ ያደርጉታል፤ 3እርሱም በምድሪቷ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከትን ቢነፋ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፥ 4የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ሰይፍ መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። 5የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ነፍሱን ባዳነ ነበር። 6ዘበኛው ግን ሰይፍ ሲመጣ አይቶ መለከቱን ባይነፋ፥ ሕዝቡን ባያስጠነቅቅ፥ ሰይፍም መጥቶ አንድ ሰው ከእነርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኃጢአቱ ተወስዶአል ደሙን ግን ከዘበኛው እጅ እፈልጋለሁ።
7አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ዘበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 8ኃጢአተኛውን ሰው፦ ኃጢአተኛ ሆይ፥ በእርግጥ ትሞታለህ በምለው ጊዜ፥ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ባታስጠነቅቀው ያ ኃጢአተኛ ሰው በኃጢአቱ ይሞታል፥ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 9ነገር ግን ከመንገዱ እንዲመለስ ኃጢአተኛውን ሰው ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።
የእግዚአብሔር ፍትሕና ምሕረት
10አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ቤት፦ እናንተ፦ በደላችንና ኃጢአታችን በላያችን አሉ በእነርሱም እየመነመንን ነው፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። 11በሕያውነቴ እምላለሁ ኃጢአተኛው ሰው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ኃጢአተኛው እንዲሞት አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። 12አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፥ ኃጢአተኛም ከኃጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኃጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኃጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። 13እኔ ጻድቁን፦ በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁት ጊዜ፥ እርሱ ጽድቁን ተማምኖ ኃጢአት ቢሠራ በሠራው ኃጢአትም ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። 14እኔም ኃጢአተኛውን ሰው፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ እርሱ ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፥ 15ኃጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ፥ የነጠቀውንም ቢመልስ፥ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ ኃጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 16የሠራው ኃጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአል፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።
17የሕዝብህም ልጆች፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። 18ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአትን ቢሠራ በእነርሱ#33፥18 በሠራቸው ኃጢአቶች ይሞታል። ይሞታል። 19ኃጢአተኛውም ከኃጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ በእነርሱ በሕይወት ይኖርበታል። 20እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።
የኢየሩሳሌም ውድቀት
21 #
2ነገ. 25፥3-10፤ ኤር. 39፥2-8፤ 52፥4-14። እንዲህም ሆነ፥ በተማረክን በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፦ ከተማይቱ ተመታች አለኝ። 22ያመለጠው ሰው ከመምጣቱ በፊት በነበረው ምሽት የጌታ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፥ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ ከዚያም በኋላ ዲዳ አልሆንሁም።
በይሁዳ ውስጥ የተረፉት
23የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24የሰው ልጅ ሆይ፥ በእስራኤል ምድር ባሉ ፍርስራሽ ስፍራዎች የሚኖሩ፦ አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ደግሞ ብዙዎች ነን ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። 25ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከደም ጋር ትበላላችሁ፥ ዓይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፥ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 26ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፥ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፥ ሁሉም ወንድ የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአል፤ ታዲያ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 27እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በፍርስራሽ ስፍራዎች ያሉት በሰይፍ ይወድቃሉ፥ በሜዳ ያሉትን መብል እንዲሆን ለአራዊት እሰጠዋለሁ፥ በምሽጎችና በዋሻዎች ያሉት በቸነፈር ይሞታሉ። 28ምድሪቱን ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይቀራል፥ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ። 29በሰሩትም ርኩሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ በማደርግበት ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
30አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤቶቻቸው ደጃፍ ስለ አንተ ይናገራሉ፥ አንዱ ከአንዱ ጋር፥ እያንዳንዱ ከወንድሙ ጋር እንዲህ ይላሉ፦ ኑ ከጌታ የመጣው ቃል ምን እንደሆነ እንስማ። 31ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፥ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፥ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ብዙ ፍቅር ይገልጣሉ፥ ልባቸው ግን ያልተገባ ጥቅማቸውን ይከተላልና። 32እነሆ አንተ እንደ ጥሩ ዘፈን፥ እንደ መልካም ድምፅ፥ እንደ ጎበዝ ተጫዋች ሆነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። 33ይህም በመጣም ጊዜ፥ እነሆ ይመጣል! ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 33: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ