ትንቢተ ሕዝቅኤል 35
35
ፍርድ በሴይር ተራራ ላይ
1 #
ኢሳ. 34፥5-17፤ 63፥1-6፤ ኤር. 49፥7-22፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ አሞጽ 1፥11፤12፤ አብ. 1፥1-14፤ ሚል. 1፥2-5። የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ሴይር ተራራ አድርግ፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ 3እንዲህም በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄን እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ። 4ከተሞችህን ፍርስራሽ አደርጋቸዋለሁ፥ አንተም ባድማ ትሆናለህ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃለህ። 5የዘለዓለም ጥል ስላለህ በመጨረሻው የፍርዳቸው ጊዜ፥ በመከራቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በሰይፍ እጅ ጥለሃቸዋልና፥ 6ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ ለደም አሳልፌ እሰጥሃለሁ ደምም ያሳድድሃል፥ ደምን ስላልጠላህ ደም ያሳድድሃል። 7የሴይርን ተራራ ውድማና ባድማ አደርገዋለሁ፥ የሚሄደውንና የሚመለሰውንም ከእርሱ አጠፋለሁ። 8ተራሮቹንም በተገደሉት ሰዎች እሞላለሁ፤ በኮረብቶችህ፥ በሸለቆዎችህና በውሃ መውረጃዎችህ ሁሉ ላይ በሰይፍ የተገደሉት ይወድቃሉ። 9ለዘለዓለም ባድማ አደርግሃለሁ፥ ከተሞችህም ሰው አይኖርባቸውም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
10ጌታ በዚያ ሳለ፥ አንተ ግን፦ “እነዚህ ሁለቱ ሕዝቦችና እነዚህ ሁለቱ አገሮች ለእኔ ይሆናሉ እኛም እንወርሳቸዋለን” ብለሃልና፥ 11ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እነርሱን ጠልተህ እንዳደረግኸው እንደ ቁጣህና እንደ ቅናትህ መጠን አደርጋለሁ፤ በፈረድሁብህም ጊዜ በእነርሱ መካከል ማንነቴን አስታውቃለሁ። 12በእስራኤል ተራሮች ላይ “ፈርሰዋል እንድንበላቸው ለእኛ ተሰጥተዋል” ብለህ የተናገርኸውን ስድብ ሁሉ እኔ ጌታ እንደ ሰማሁት ታውቃለህ። 13በአፋችሁ ታበያችሁብኝ፥ ንግግራችሁንም በእኔ ላይ አበዛችሁ፤ እኔም ሰምቼዋለሁ። 14ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምድር ሁሉ ስትደሰት አንተን ባድማ አደርግሃለሁ። 15የእስራኤል ቤት ርስት ባድማ በመሆኑ እንደተደሰትህ፥ እንዲሁ አደርግብሃለሁ፤ የሴይር ተራራ ሆይ፥ አንተ፥ ኤዶም ሁሉና ሁለንተናዋ ባድማ ትሆናላችሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 35: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ