ትንቢተ ሕዝቅኤል 37
37
የደረቁ አጥንቶች የተከማቹበት ሸለቆ
1የጌታ እጅ በላዬ ነበረ፥ ጌታም በመንፈሱ አወጣኝ፥ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ እሱም አጥንቶች ሞልተውበት ነበር። 2በእነርሱ ላይ በዙሪያቸው አሳለፈኝ፤ እነሆ በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፤ እነሆም፥ በጣም የደረቁ ነበሩ። 3እንዲህም አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” እኔም “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ” አልሁ። 4እርሱም እንዲህ አለኝ፦ በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፥ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ፥ የጌታን ቃል ሰሙ። 5ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በእናንተ ላይ እስትንፋስ#37፥5 ዕብራይስጡ “ሩሓ” የሚለው ትንፋሽ፥ ንፋስ ወይም መንፈስ የሚል ትርጒም አለው። አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላላችሁ። 6ጅማትንም አደርግላችኋለሁ፥ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ ቆዳ አለብሳችኋለሁ፥ በውስጣችሁ እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
7እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢትንም ስናገር እነሆ የመንኰሻኰሽ ድምፅ ነበር፥ አጥንት ከአጥንቱ ጋር እየሆነ አጥንቶች አንድ ላይ ሆኑ። 8እኔም አየሁ፥ እነሆ ጅማትና ሥጋ ነበረባቸው፥ ቆዳም ከላይ እስከ ታች ሸፈናቸው፥ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም። 9እንዲህም አለኝ፦ “ትንቢት ተናገር፥ ለነፋስ ትንቢት ተናገር የሰው ልጅ ሆይ፥ ነፋሱንም እንዲህ በለው፦ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ፥ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፥ በሕይወት እንዲኖሩ በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።’” 10#ራእ. 11፥11።እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፥ እስትንፋስም በውስጣቸው ገባ፥ ሕያዋንም ሆኑ፥ እጅግ በጣም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
11እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ አጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው፤ እነሆ፦ “አጥንቶቻችን ደርቀዋል ተስፋችንም ጠፍቶአል፤ ፈጽመን ተቆርጠናል” ይላሉ። 12ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፥ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣችኋለሁ። 13ሕዝቤ ሆይ፥ መቃብራችሁን ስከፍት ከመቃብራችሁም ሳወጣችሁ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 14መንፈሴን በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁ አስቀምጣችኋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደ ተናገርሁ፥ እንዳደረግሁትም ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ።
ሁለቱ በትሮች
15የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 16አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ አንድ በትር ለራስህ ውሰድ፥ በላዩ “ለይሁዳና ለተባባሪዎቹ የእስራኤል ልጆች” ብለህ ጻፍበት፤ ሌላም በትር ውሰድ፦ በላዩም “የኤፍሬም በትር ለሆነው ለዮሴፍና ለተባባሪዎቹ፥ ለመላው የእስራኤል ቤት” ብለህ ጻፍበት። 17በእጅህ ውስጥ አንድ በትር እንዲሆኑ አንዱ ከአንዱ ጋር አጋጥመህ ያዛቸው። 18የሕዝብህ ልጆች፦ “እነዚህ ለአንተ ምን እንደ ሆኑ አትነግረንምን?” ሲሉህ፥ 19እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በኤፍሬም እጅና በተባባሪዎቹ በእስራኤል ነገዶች ያለውን የዮሴፍን በትር እወስዳለሁ፥ ከይሁዳ በትር ጋር አስቀምጣቸዋለሁ፥ አንድ በትር አደርጋቸዋለሁ፥ በእጄም አንድ ይሆናሉ። 20በላያቸው የምትጽፍባቸው በትሮች በዓይናቸው ፊት በእጅህ ይሆናሉ። 21አንተም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ሕዝቦች መካከል እወስዳለሁ፥ ከየስፍራውም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። 22በምድሪቱ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥ ለሁሉም ንጉሥ ይሆናል፤ ዳግመኛ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፥ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥቶች ሆነው አይከፈሉም። 23በጣዖቶቻቸው፥ በአጸያፊ ነገሮቻቸውና በመተላለፋቸው ሁሉ ዳግመኛ አይረክሱም፤ ኃጢአት ከሠሩባቸው መኖሪያ ቤቶቻቸው ሁሉ አድናቸዋለሁ፥ አነጻቸዋለሁም፤ እነርሱ ለእኔ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።
24 #
ሕዝ. 34፥24። አገልጋዬ ዳዊት ንጉሥ ይሆናቸዋል፤ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል፤ በፍርዴ ይሄዳሉ፥ ትእዛዜን ይጠብቃሉ ይፈጽሟቸዋልም። 25ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት፥ አባቶቻችሁም በኖሩባት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱ፥ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ለዘለዓለም በእርሷ ይኖራሉ፤ አገልጋዬ ዳዊት ለዘለዓለም ልዑላቸው ይሆናል። 26የሰላም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፥ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ አጸናቸዋለሁ፥ አበዛቸዋለሁ፥ መቅደሴንም በመካከላቸው ለዘለዓለም አኖራለሁ። 27#2ቆሮ. 6፥16፤ ራእ. 21፥3።ማደሪያዬ በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፥ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 28መቅደሴም ለዘለዓለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እስራኤልን የቀደስኩ እኔ ጌታ እንደሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 37: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ