ትንቢተ ሕዝቅኤል 4
4
የኢየሩሳሌም መከበብ በስዕል እንደ ተገለፀ
1አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለራስህ ጡብን ውሰድ፥ በፊትህም አኑራት፥ በላይዋ ላይም የኢየሩሳሌምን ሥዕል ሳልባት፤ 2ክበባት፥ ምሽግም ሥራባት፥ ቁልልም ሥራባት፥ ሰፈርም አቁምባት፥ በዙሪያዋም ቅጥርን የሚያፈርስ ግንድ አድርግባት። 3የብረት ምጣድም ውሰድ፥ በአንተና በከተማይቱ መካከል የብረት ቅጥር አድርገው፥ ፊትህንም ወደ እርሷ አቅና፥ የተከበበችም ትሆናለች፥ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።
4አንተም በግራ ጐንህ ተኛ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት አኑርባት፥ በምትተኛበትም ቀኖች ቍጥር ኃጢአታቸውን ትሸከማለህ። 5እኔም የኃጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀኖች ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፥ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ። 6እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ ድጋሚ በቀኝ ጐንህ ትተኛለህ፥ የይሁዳንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፥ አንድን ዓመት እንደ አንድ ቀን አድርጌ አርባ ቀን ሰጥቼሃለሁ። 7ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ፊትህን ታዞራለህ፥ ክንድህን ዕራቁቱን አድርገህ ትንቢትን ትናገርባታለህ። 8እነሆም ገመድ አደርግብሃለሁ፥ የምትከበብበትንም ቀኖች እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጎንህ ወደ ሌላው ጎንህ አትገላበጥም።
9አንተም ለራስህ ስንዴና ገብስ፥ ባቄላና ምስር፥ ማሽላና አጃን ውሰድ፥ በአንድ ዕቃ ውስጥ አድርጋቸው፥ ለራስህም ምግብ አዘጋጅ፥ በጎንህ እንደ ምትተኛበት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ። 10የምትመገበውም ምግብ በሚዛን በየቀኑ ሃያ ሰቅል ይሁን፥ በየጊዜውም ትበላለህ። 11ውኃም በልክ ትጠጣለህ፥ የኢን መስፈሪያ አንድ ስድስተኛ ትጠጣለህ፥ በየጊዜውም ትጠጣለህ። 12እንደ ገብስ እንጐቻ አድርገህም ትበላዋለህ፥ ከሰውም በሚወጣ ፋንድያ በፊታቸው ትጋግረዋለህ። 13ጌታም እንዲህ አለ፦ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ርኩስ ምግባቸውን በምበትንባቸው አገሮች መካከል ይበላሉ። 14እኔም እንዲህ አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወይኔ! እነሆ፥ ሰውነቴ#4፥14 ዕብራይስጡ ነፍሴ ይለዋል። አልረከሰችም፥ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ፥ የሞተ ወይም እንስሳ የገደለውን ከቶ አልበላሁም፥ ርኩስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም። 15እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ተመልከት በሰው ፋንድያ ፈንታ ኩበት ሰጥቼሃለሁ፥ ምግብህንም በእርሱ አዘጋጅ። 16ደግሞም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ እኔ በኢየሩሳሌም የምግብን በትር እሰብራለሁ፥ ምግብ እየፈሩ በሚዛን ይበላሉ፥ ውኃም እየደነገጡ በልክ ይጠጣሉ፤ 17ይህም ምግብና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲደነቁ፥ በኃጢአታቸውም እንዲመነምኑ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ