የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 44

44
የተዘጋው በር
1ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። 2ጌታም እንዲህ አለኝ፦ ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል፤ አይከፈትምም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል። 3መስፍኑ ብቻ በጌታ ፊት ምግብ ለመብላት ይቀመጥበታል፤ በበሩ መተላለፊያ መንገድ ይገባል በዚያም መንገድ ይወጣል።
ወደ መቅደሱ ስለመግባት
4በሰሜኑ በር መንገድ ወደ ቤቱ ፊት ለፊት አገባኝ፤ እኔም አየሁ፥ እነሆ የጌታ ክብር የጌታን ቤት ሞልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 5ጌታም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጌታ ቤት ሥርዓት ሁሉ እና ሕጉን ሁሉ የምናገርህን ሁሉ ልብ አድርግ በዓይንህ ተመልከት በጆሮህም ስማ፤ የቤቱን መግቢያ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ። 6ለዓመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ርኩሰታችሁ ከእንግዲህ ሁሉ ያብቃ፥ 7ምግቤን፥ ስብንና ደምን፥ በምታቀርቡበት ጊዜ ቤቴን እንዲያረክሱ በመቅደሴ ውስጥ እንዲሆኑ ያልተገረዘ ልብ፥ ያልተገረዘ ሥጋ ያላቸውን ባዕዳንን አግብታችኋል፥ በርኩሰታችሁም ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋል። 8በመቅደሴ ውስጥ ሥርዓቴን ጠባቂዎች ለራሳችሁ አስቀመጣችሁ እንጂ የተቀደሰውን ነገሬን ሥርዓት አልጠበቃችሁም።
9ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ልጆች መካከል ያለ የባዕድ ልጅ ሁሉ፥ ልቡ ያልተገረዘ ሥጋው ያልተገረዘ የባዕድ ልጅ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ። 10እስራኤል እኔን ከመከተል ርቀው በተቅበዘበዙ ጊዜ፥ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ የራቁት ሌዋውያን ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። 11በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች፥ በቤቱም በሮች ዘበኞች ይሆናሉ፥ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና መሥዋዕትን ያርዳሉ፥ ሊያገለግሉአቸውም በፊታቸው ይቆማሉ። 12በጣዖቶቻቸው ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኃጢአት ዕንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13በክህነት ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ አይቀርቡም፥ ወደተቀደሰው ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አይቀርቡም፤ ስድባቸውንና የሠሩትን ርኩሰታቸውን ይሸከማሉ። 14ሆኖም ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዓት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ።
ስለ ሌዋውያን ካህናት
15የእስራኤል ልጆች ከእኔ በራቁ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ሊያገለግሉኝ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙን ወደ እኔ ሊያቀርቡ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16ወደ መቅደሴም ይገባሉ እኔን ለማገልገል ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ ሥርዓቴን ይጠብቃሉ። 17#ዘፀ. 28፥39-43፤ ዘሌ. 16፥4።ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛው አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ ባገለገሉ ጊዜ አንዳች የበግ ጠጉር በላያቸው አይሁን። 18በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፥ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያልብ ነገር አይታጠቁ። 19#ዘሌ. 16፥23።ወደ ውጭው አደባባይ ወደ ሕዝቡ በሚወጡበት ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ፥ በተቀደሰው ቤት ውስጥ ያኑሩት፥ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላ ልብስ ይልበሱ።
20 # ዘሌ. 21፥5። ራሳቸውን አይላጩ፥ የተያዘ ጠጉራቸውንም አይልቀቁትም፥ ነገር ግን የራሳቸውን ጠጉር ይከርከሙ። 21#ዘሌ. 10፥9።ካህናቱ ሁሉ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ አይጠጡ። 22#ዘሌ. 21፥7፤13፤14።መበለቲቱንና የተፈታችውን ለሚስትነት አይውሰዱ፤ነገር ግን ከእስራኤል ቤት ዘር የሆነችውን ድንግል ወይም የካህን ሚስት የነበረችውን መበለት ይውሰዱ። 23#ዘሌ. 10፥10።ሕዝቤን ቅዱስ በሆነውና በረከሰው መካከል እንዲለዩ ያስተምሩ፥ ንጹሕ በሆነውና ንጹሕ ባልሆነው መካከል እንዲለዩ ያሳዩአቸው። 24ክርክር በሚነሣበት ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ በፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዓቴን ይጠብቁ፥ ሰንበታቴንም ይቀድሱ። 25#ዘሌ. 21፥1-4።እንዳይረክሱ ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት ወይም ለእናት ወይም ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ ወይም ለወንድም ወይም ላላገባች እኅት ይርከሱ። 26ከነጻ በኋላ ሰባት ቀን ይቁጠሩለት። 27በመቅደስም ውስጥ ሊያገለግል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቅርብ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
28 # ዘኍ. 18፥20። ርስት ይሆንላቸዋል፤ ርስታቸው እኔ ነኝ፤ በእስራኤልም ግዛት አትስጡአቸው፤ ግዛታቸው እኔ ነኝ። 29#ዘኍ. 18፥8-19።የእህሉን ቁርባን፥ የኃጢአትን መሥዋዕትና የበደልን መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም እርም#44፥29 ለእግዚአብሔር የተለየ። የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል። 30የበኩራቱ ሁሉ መጀመሪያ፥ ስጦታ ሁሉ፥ ስጦታዎቻችሁ ሁሉ፥ ለካህናት ይሆናል፤ በቤትህም ውስጥ በረከት እንዲያድር የሊጣችሁን በኵራት ለካህን ትሰጣላችሁ። 31#ዘሌ. 22፥8።ካህናቱ የሞተ ወይም ሌላ አውሬ የገደለውን ወፍ ወይም እንስሳ አይብሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ