ትንቢተ ሕዝቅኤል 46
46
አንዳንድ ሕጎች
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በውስጠኛው አደባባይ ፊቱ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ይዘጋ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀን ይከፈት እንዲሁም በወር መባቻ ቀን ይከፈት።
2መስፍኑ ከውጭ በኩል ባለው በር በመተላለፊያ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፥ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቅርቡ፥ እርሱም በበሩ መድረክ ላይ ይስገድ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፥ በሩ ግን እስከ ማታ ድረስ አይዘጋ። 3የምድሪቱ ሕዝብ በዚያ በር መግቢያ በሰንበታትና በመባቻ በጌታ ፊት ይስገዱ። 4መስፍኑ በሰንበት ቀን ለጌታ የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸው ስድስት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለበት አንድ አውራ በግ ይሁን፤ 5ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን ይሁን፥ ለእያንዳንዱም ጠቦት እጁ የሰጠችውን ያህል የእህል ቁርባን ይሁን፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። 6በመባቻ ቀን ከመንጋው ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን፥ ነውር የሌለባቸውንም ስድስት ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ 7ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ለአውራው በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ የእህል ቁርባን ያቅርብ፥ ለጠቦቶቹም እጁ የቻለችውን ያህል፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። 8መስፍኑ በሚገባበት ጊዜ በበሩ መተላለፊያ መንገድ ይግባ በዚያው መንገድ ይውጣ።
9የምድሪቱ ሕዝብ ግን በየክብረ በዓሉ ቀን ወደ ጌታ ፊት በመጡ ጊዜ በሰሜን በር በኩል ሊሰግድ የገባው በደቡብ በር በኩል ይውጣ፥ በደቡብ በር የገባው በሰሜን በር በኩል ይውጣ፤ በፊት ለፊት ባለው ይውጣ እንጂ በገባበት በር አይመለስ። 10በመካከላቸው ያለው መስፍን በሚገቡበት ጊዜ ይግባ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ። 11በበዓላትና በክብረ በዓል ቀኖች የእህሉ ቁርባን ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እጁ የሰጠችውን ያህል፥ ለኢፍ መስፈሪያም አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይሆናል። 12መስፍኑ በፈቃዱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ወይም የሰላሙን መሥዋዕት፥ በፈቃዱ ለጌታ የሚያቀርበውን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ፥ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት፥ በሰንበትም ቀን እንደሚያደርግ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚያ በኋላ ይውጣ፥ ከወጣም በኋላ በሩ ይዘጋ።
13በየዕለቱም ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት በግ ጠቦት ለጌታ ያቅርብ፤ ማለዳ ማለዳም ያቅርበው። 14ከእርሱም ጋር አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ መልካም ዱቄትን መለወሻም የሚሆን በኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት ማለዳ ማለዳ የእህልን ቁርባን ያቅርብ፤ ይህ የእህል ቁርባን ዘወትር ለጌታ የሚቀርብ ለዘለዓለሙ ሥርዓት ይሁን። 15እንዲሁም ዘወትር ለሚቃጠለው መሥዋዕት ጠቦቱን፥ የእህሉን ቁርባንና ዘይቱን ማለዳ ማለዳ አቅርቡ።
16ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መስፍኑ ከልጆቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ ለልጆቹ ይሁን፤ በውርስም ይዞታቸው ይሆናል። 17#ዘሌ. 25፥10።ነገር ግን ከባርያዎቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ እስከ ነጻነት ዓመት ድረሰ ለእርሱ ይሁን፥ ከዚያም በኋላ ለመስፍኑ ይመለስለት፤ ርስቱ ለልጆቹ ብቻ ይሁን። 18መስፍኑ ሕዝቡን ከይዞታቸው ሊጨቁናቸው ርስታቸውን አይውሰድባቸው፤ ሕዝቤ ሁሉ ከይዞታቸው እንዳይነቀሉ ከገዛ ይዞታው ለልጆቹ ርስትን ይስጥ።
19በበሩ አጠገብ ባለው መግቢያ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ለካህናት ወደሚሆን ወደተቀደሰው ክፍል አገባኝ፤ እነሆ በዚያ በምዕራብ በኩል በስተ ኋላ አንድ ስፍራ ነበረ። 20እንዲህም አለኝ፦ “ካህናቱ ሕዝቡን ለመቀደስ ወደ ውጭው አደባባይ እንዳያወጡ የበደሉን መሥዋዕትና የኃጢአቱን መሥዋዕት የሚቀቅሉበት፥ የእህሉንም ቁርባን የሚጋግሩበት ስፍራ ይህ ነው።”
21ወደ ውጭው አደባባይ አወጣኝ በአደባባይም ወዳለው ወደ አራቱ ማዕዘን አዞረኝ፤ እነሆ በእያንዳንዱ የአደባባይ ማዕዘን አደባባይ ነበረ። 22በአደባባዩ በአራቱ ማዕዘን ርዝመቱ አርባ ክንድ ወርዱም ሠላሳ ክንድ የሆነ የታጠረ አደባባይ ነበረ፤ በአራቱም ማዕዘን ያሉት እኩል ነበሩ። 23በአራቱም ዙሪያ ግንብ ነበረ፥ በግንቡም ሥር በዙሪያው የመቀቀያ ቦታ ነበረ። 24እንዲህም አለኝ፦ “እነዚህ የቤቱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚቀቅሉባቸው ስፍራዎች ናቸው።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 46: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ