ኦሪት ዘፍጥረት 31
31
ያዕቆብ ሽሽት
1ያዕቆብም፥ የላባ ልጆች፦ “ያዕቆብ የአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፥ የአባታችን ከነበረውም ይህንም ሁሉ ሀብት አገኘ” ሲሉ ሰማ። 2እንደ ቀድሞው በላባ ተወዳጅ አለመሆኑን ያዕቆብም አየ። 3በዚህን ጊዜ ጌታ ያዕቆብን፥ “ወደ አባቶችህ ምድር እና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፥ ከአንተም ጋር እሆናለሁ” አለው። 4ያዕቆብም ላከና ራሔልንና ልያን በጎቹ ወደ ነበሩበት መስክ ጠራቸው፥ 5እንዲህም አላቸው፥ “አባታችሁ ከእኔ ጋር እንደ ቀድሞው እንደማይወደኝ አያለሁ፥ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው። 6እኔ ባለኝ ጉልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልኩ እናንተም ታውቃላችሁ። 7አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም ዐሥር ጊዜ ለወጠ፥ እግዚአብሔር ግን ይጎዳኝ ዘንድ አልፈቀደለትም። 8‘ዝንጉርጉሮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ቢለኝ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ዝንጉርጉሮችን ወለዱ፤ ደግሞም ‘ሽመልመሌ መሳዮቹ ሁሉ ለአንተ ደመወዝ ይሁኑ’ ቢለኝ፥ መንጋዎቹ ሁሉ ሽመልመሌ ወለዱ። 9እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ። 10በመንጋዎቹ መራቢያ ወራት ዐይኖቼን አነሳሁ፥ በሕልምም በበጎቹ ላይ የሚንጠላጠሉት አውራ ፍየሎች ሽመልመሌ፥ ዝንጉርጉርና ነቊጣ እንደ ነበሩ አየሁ። 11የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም፦ ያዕቆብ ሆይ አለኝ፥ እኔም፦ እነሆኝ አልሁት። 12እርሱም እንዲህ አለኝ፥ ‘ዓይንህን አቅናና እይ፥ መንጋዎቹ ላይ የሚንጠላጠሉት ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ፥ ዝንጉርጉሮች እና ነቊጣ ናቸው፤ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና። 13#ዘፍ. 28፥18-22።ሐውልት የቀባህበት እና ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፥ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ ምድር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።’” 14ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት፥ “በአባታችን ቤት ለእኛ አንዳች ድርሻ ወይም ርስት አለን? 15እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልኮ። 16ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፥ እንግዲያውስ አሁንም፥ እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ፥ አድርግ።”
17ከዚያም ያዕቆብ ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤ 18መንጎቹንም ሁሉ፥ ያፈራውን ንብረት ሁሉ፥ ፓዳን-ኣራም ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ። 19ላባም በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፥ ራሔልም የአባትዋን ቤት ጣዖቶች#31፥19 ዕብራይስጥ፥ ተራፊም ሰረቀች። 20ያዕቆብም ለመሄድ ማቀዱን ሳይነግረው ሶርያዊውን ላባን ከድቶ ኮበለለ። 21እርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፥ ተነሥቶም የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ኮረብታማው አገር ገለዓድ አቀና።
የላባ ያዕቆብን መከታተል
22በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ሲነገረው፥ 23ከዘመዶቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ ከዚያም በገለዓድ ተራራማ አገር ላይ አገኛቸው። 24እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ፥ “ያዕቆብን፥ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው። 25ላባም ያዕቆብን ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን ኮረብታማው አገር ተክሎ ነበር፥ ላባም ከዘመዶቹ ጋር በገለዓድ ኮረብታማው አገር ድንኳኑን ተከለ። 26ላባም ያዕቆብን አለው፥ “የፈጸምከው ምንድነው? እኔን አታልልከኝ፥ ልጆቼንስ እንደ ሰይፍ ምርኮኛ ለምን ወሰድካቸው? 27ስለምን በስውር ሸሸህ፥ እኔንም አታለልከኝ፥ በደስታና በዘፈንም በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም? 28ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና#31፥28 አላዋቂነት። አደረግህ። 29ጉዳት አደርስብህ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፥ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት፥ ‘ያዕቆብን ክፉም ሆነ ደግ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ ብሎ ነገረኝ። 30አሁንም የአባትህን ቤት እጅጉን ናፍቆሃልና ሂድ፥ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?” 31ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው፥ “ልጆችህን በጉልበት ከእኔ የምትቀማኝ ስለ መሰለኝና ስለ ፈራሁ ይህን አደረግሁ። 32አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፥ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደሆነ በዘመዶቻችን ፊት ፈልግ፥ ውሰደውም” አለ። ያዕቆብ ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው አያውቅም ነበር።
33ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን ወደ ሁለቱም ባርያዎች ድንኳን ገባ፥ ነገር ግን አላገኘም። ከልያም ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ። 34ራሔልም ተራፊምን ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፥ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፥ አንዳችም አላገኘም። 35እርሷም አባትዋን፥ “ፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ አትቆጣብኝ፥ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ#31፥35 የወር አበባ። ደርሶብኛልና” አለችው። እርሱም ፈለገ፥ ነገር ግን ተራፊምን አላገኘም።
36ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፥ ያዕቆብም ላባንም እንዲህ አለው፥ “ምን በደልሁህ? ይህን ያህል ያሳደድኸኝ፥ ኃጢአቴስ ምንድነው? 37አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፥ የቤትህስ ሁሉ የሆነ ዕቃ ምን አገኘህ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በዘመዶቼና በዘመዶችህ ፊት አቅርበው። 38ለሃያ ዓመታት ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፥ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ 39አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፥ እኔው ራሴ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፥ በቀን ሆነ በሌሊት ቢሰረቅ፥ ያን ከእጄ ትፈልግ ነበር። 40እንዲህ ስሆን፥ የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር ይበላኝ ነበር፥ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ። 41እነዚህን ሃያ ዓመታት በአንተ ቤት ነበርሁ፥ ዐሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ስድስት ዓመትም ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፥ ደመወዜንም ዐሥር ጊዜ ለዋወጥኸው። 42የአባቴ አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት፥ ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ፥ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፥ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ልፋት አየ፥ ትናንትና ሌሊትም ገሠጸህ።”
የያዕቆብ እና ላባ ስምምነት
43ላባም ለያዕቆብ መልሶ እንዲህ አለው፥ “ሴቶቹ ልጆች ልጆቼ ናቸው፥ ሕፃናቱም ሕፃናቴ ናቸው፥ መንጎቹም መንጎቼ ናቸው፥ የምታየውም ሁሉ የእኔ ነው። ነገር ግን ዛሬ በእነዚህ በሴቶች ልጆቼና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ላደርግ እችላለሁ? 44አሁንም ና፥ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፥ በእኔና በአንተ መካከልም ምስክር ይሁን።” 45ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ። 46ያዕቆብም ዘመዶቹን “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው፥ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፥ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ። 47ላባም “ይጋር ሠሀዱታ”#31፥47 ይጋርሣሀዱታ፦ በሶርያ ቋንቋ “የምስክር ካብ” ወይም “ሐውልት” ማለት ነው። ብሎ ጠራት፥ ያዕቆብም “ገለዓድ”#31፥47 ገለዓድ፦ በዕብራይስጥ “የምስክር ካብ” ወይም “ሐውልት” ማለት ነው። አላት። 48ላባም፥ “ይህ ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለ። ስለዚህም ገለዓድ ብሎ ሰየማት፥ 49ደግሞም “ምጽጳ”#31፥49 ምጽጳ፦ በዕብራይስጥ “መጠበቂያ” ማለት ነው።፥ “እኛ አንዳችን ከሌላው በተለያየን ጊዜ ጌታ በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይጠብቅ” ብሏልና። 50“ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ሚስቶችን ብታገባባቸው፥ ማንም ሰው ከእኛ ጋር ባይኖር እንኳን፥ በእኔና በአንተ መካከል እግዚአብሔር ምስክር ነው።” 51ላባም ያዕቆብን አለው፥ “በእኔና በአንተ መካከል ይህ ክምር፥ ያቆምኩት ሐውልትም እነሆ፥ 52እኔ ወደ አንተ ይህን ክምር እንዳላልፍ፥ አንተም ለክፋት ወደ እኔ ይህን ክምርና ይህን ሐውልት እንዳታልፍ፥ ይህ ክምር እና ይህ ሐውልት ምስክር ነው። 53የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ፥ የአባታቸውም አምላክ፥ በእኛ መካከል ይፍረድ።” ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት ማለ። 54ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን አቀረበ፥ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጠራ፥ እነርሱም ምግብ ተመገቡ፥ በዚያም በተራራ ሌሊቱን ሙሉ አሳለፉ። 55ጠዋት በማለዳ ላባ ተነሥቶ የልጅ ልጆቹን እና ሴቶቹን ልጆቹን ሳመ ባረካቸውም፥ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 31: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ