ኦሪት ዘፍጥረት 34
34
የዲና መደፈር
1የልያ ልጅ ዲናም፥ የዚያን አገር ሴት ልጆችን ለማየት ወጣች። 2የአገሩ ገዢ የሒዋዊው ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፥ ወሰዳትም ከእርሷም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም። 3ነፍሱም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈች፥ ልጅቱንም አፈቀራት፥ እርሷንም በአፍቅሮት አናገራት። 4ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፥ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው። 5ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፥ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በመስክ ተሰማርተው ነበር፥ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ።
ከሴኬማውያን ጋር የተደረገ የጋብቻ ስምምነት
6የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ። 7የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከመስክ መጡ፥ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ኀፍረትን ስላደረገ አዘኑ፥ እንዲህ አይደረግምና እጅግም ተቈጡ። 8ሐሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው፥ “ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ነፍሱ ተወስዳለችና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርሷን ስጡት። 9ከእኛም ጋር በጋብቻ ተሳሰሩ፥ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ። 10ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም እንደፈለጋችሁ ሁኑባት፥ ኑሩባት፥ ነግዱባትም፥ ሀብትም አፍሩባት።” 11ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ፥ “በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ። 12ብዙ ጥሎሽና ስጦታ አምጣ በሉኝ፥ ይህችን ልጅ እንዳገባ ስጡኝ እንጂ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ።” 13የያዕቆብም ልጆች፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፥ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ። 14እንዲህም አሉአቸው፦ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፥ ይህ ነውር ይሆንብናልና። 15እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፥ 16ሴቶች ልጆቻችንንም እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፥ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን። 17ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።”
18ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ። 19ወጣቱም ልጅ፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፥ ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም። እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ። 20ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ፦ 21“እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፥ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፥ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ። 22ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፥ እርሱም እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ ነው። 23ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ።” 24ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን “እሺ” አሉ፥ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።
የስምዖን እና ሌዊ በቀል
25ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው እያሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፥ 26ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ። 27የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፥ 28በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ። 29ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ። 30ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ፦ “በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፥ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፥ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፥ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።” 31እነርሱም፦ “በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ሊደረግ ይገባልን?” አሉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 34: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ