የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 39

39
የዮሴፍ በግብጽ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት
1በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፥ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። 2#የሐዋ. 7፥9።ጌታ ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። 3አሳዳሪውም ጌታ ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወነለት ባየ ጊዜ፥ 4ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። 5ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ጌታ የግብፃዊውን ቤት ባረከ፥ የጌታም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። 6ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፥ ማናቸውንም ጉዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤
ዮሴፍን የማማለል ሙከራ
7እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፥ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው። 8እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። 9በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፥ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እሠራለሁ?” 10ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጉተውም፥ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛቱ ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም። 11አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። 12እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። 13እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፥ 14የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሮአል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤ 15ለእርዳታ መጮኼን ሲሰማም፥ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።” 16ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፥ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው። 17ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባርያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤ 18ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”
19ጌታውም “ባርያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ፥ ተቈጣ። 20ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፥ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው።
ዮሴፍ በግዞት
21 # የሐዋ. 7፥9። ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፥ ጌታ ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፥ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። 22ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። 23እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፥ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለማንኛውም ጉዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ