ኦሪት ዘፍጥረት 41
41
የፈርዖን ሕልሞች
1ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፥ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ 2እነሆ መልካቸው ያማረ፥ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። 3ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፥ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። 4እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፥ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጡአቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ። 5ፈርዖንም እንደገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፥ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፥ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። 6ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። 7የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፥ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጡአቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር። 8#ዳን. 2፥2።በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብጽ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፥ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጉምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።
9በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። 10በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። 11ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጒም ነበረው። 12በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፥ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ 13ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ።”
14ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጉሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ። 15ፈርዖንም ዮሴፍን፥ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጉምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው። 16ዮሴፍም ፈርዖንን፥ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለፈርዖን የሚሻውን ትርጒም ይሰጠዋል” አለው። 17ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። 19ከእነርሱም በኋላ፥ ዐቅመ ደካማ፥ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። 20ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፥ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። 21ከዋጧቸውም በኋላ፥ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ። 22እንደዚሁም፥ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። 23ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። 24የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።”
25ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። 26ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፥ ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። 27ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፥ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው። 28አስቀድሜ ለፈርዖን እንደተናገርኩት፥ እግዚአብሔር ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። 29በመላው የግብጽ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፥ በግብጽ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። 31ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፥ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። 32ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፥ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንንም እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል። 33እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፥ በመላው የግብጽ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። 34እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፥ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። 35እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። 36የሚከማቸው እህል፥ ወደ ፊት በግብጽ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።”
የዮሴፍ ሹመት
37ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምንቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። 38ፈርዖንም፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው። 39ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፥ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። 40#የሐዋ. 7፥10።አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።” 41ከዚያም፥ ፈርዖን ዮሴፍን “በመላዪቱ የግብጽ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው። 42#ዳን. 5፥29።ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። 43በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፥ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው። ሰዎችም በፊቱ፥ “እጅ ንሡ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው። 44ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፥ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብጽ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው። 45ፈርዖንም ዮሴፍን “ጸፍናት ፐዕናህ” ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱጠ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብጽ ምድር ተዘዋወረ።
46ዮሴፍ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፥ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብጽን ምድር በሙሉ ዞረ። 47በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች። 48በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፥ ዮሴፍ በግብጽ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ። 49ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር።
የዮሴፍ ልጆች
50ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፥ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 51ዮሴፍም፥ “እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ፥ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ አለው። 52እንደዚሁም፥ “መከራ በተቀበልኩበት ምድር እግዚአብሔር ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም አለው።
53በግብጽ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና 54#የሐዋ. 7፥11።ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፥ በመላው የግብጽ ምድር ግን ምግብ ነበር። 55#ዮሐ. 2፥5።ራቡ በመላው የግብጽ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፥ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብፃውያኑን፥ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው። 56ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለ ሄደ፥ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብጽ ጸንቶ ነበር። 57ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፥ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ምድር መጡ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 41: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ