ኦሪት ዘፍጥረት 45
45
ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ
1 #
የሐዋ. 7፥13። ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም፦ “ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፥ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ ማንም ከአጠገቡ የቆመ አልነበረም። 2ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፥ የግብጽ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ። 3ዮሴፍም ለወንድሞቹ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፥ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ አለን?” አለ። ወንድሞቹም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና፥ ሊመልሱለት አልቻሉም። 4ዮሴፍም ወንድሞቹን “እስቲ ወደ እኔ ቅረቡ” አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። 5አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፥ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ልኮኛልና። 6ይህ በምድር ላይ ሁለት ዓመት ራብ የሆነበት ነው፥ ገና የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ይመጣል። 7እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ። 8አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፥ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱምም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብጽ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ። 9#የሐዋ. 7፥14።አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው፦ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፥ ወደ እኔ ና አትዘግይ፥ 10አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ፥ ከእኔም በቅርበት፥ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ። 11በዚያም፥ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና፥ አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ።’ 12እነሆም የተናገረቻችሁ የእኔ አንደበት እንደ ሆነች የእናንተ ዐይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዐይኖች አይተዋል። 13ለአባቴም በግብጽ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፥ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።” 14የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፥ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ። 15ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፥ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ።
የፈርዖን ግብዣ
16በፈርዖንም ቤት፥ “የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፥” በሰሙትም ነገር ፈርዖንና አገልጋዮቹ ደስ ተሰኙበት። 17ፈርዖንም ዮሴፍን አለው፦ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ይህን አድርጉ፥ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከዓን ምድር ሂዱ፥ 18አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፥ እኔም የግብጽን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ።’ 19አንተም ወንድሞችህን፦ እንዲህ አድርጉ በላቸው፥ ከግብጽ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፥ 20ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብጽ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።”
ወደ ከነዓን መመለስ
21የእስራኤል ልጆችም እንደተነገራቸው አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤ 22ለእያንዳንዳቸውም አዳዲስ ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን አምስት የክት ልብስና ሦስት መቶ ብር ሰጠው። 23ለአባቱም እንደዚሁ፥ በዐሥር አህዮች የተጫነ ከግብጽ ምድር የሚገኘውን መልካም ነገር ላከለት፤ እንዲሁም በሚመጣበት ጊዜ ለስንቅ የሚሆነው በሌሎች ዐሥር እንስት አህዮች የተጫነ እህል፥ ዳቦና ምግብ ላከለት። 24ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ “በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።” 25እነርሱም ከግብጽ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ። 26እንዲህም ብለው ነገሩት፦ “ዮሴፍ ገና በሕይወቱ አለ፥ እርሱም በግብጽ ምድር ላይ ሁሉ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ ሊያምናቸውም አልቻለም። 27ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ 28እስራኤልም፦ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፥ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 45: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ