ኦሪት ዘፍጥረት 48
48
ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች መባረኩ
1ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ተነገረው፤ ስለዚህ ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ያዕቆብን ለማየት ሄደ። 2ለያዕቆብም፦ “እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል” ብለው ነገሩት፥ እስራኤልም ሰውነቱን አበረታቶ፥ በአልጋው ላይ ተቀመጠ። 3#ዘፍ. 28፥13፤14።ያዕቆብ ዮሴፍን አለው፦ “ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም 4ደግሞም፦ ‘እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፥ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘለዓለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ።’” አለኝ። 5አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብጽ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፥ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው። 6ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፥ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ። 7#ዘፍ. 35፥16-19።እኔም ፓዳን በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት መንገድ ቀርቶኝ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፥ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ ቀበርኋት፥ እርሷም ቤተልሔም ናት።
8እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ፦ “እነዚህ እነማን ናቸው?” አለው። 9ዮሴፍም ለአባቱ፦ “እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው” አለ። እርሱም፦ “እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ” አለ። 10የእስራኤልም ዐይኖች ከሽምግልና የተነሣ ደክመው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም። 11እስራኤልም ዮሴፍን፦ “ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፥ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ” አለው። 12ዮሴፍም ከጉልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ። 13ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው። 14እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፥ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኩር ነበርና። 15ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ 16ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፥ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፥ በምድርም መካከል ይብዙ።” 17ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፥ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። 18ዮሴፍም አባቱን፦ “አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኩሩ ይህ ነውና፥ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ” አለው። 19አባቱም እንዲህ ሲል እንቢታውን ገለጸ፦ “አውቄአለሁ ልጄ ሆይ፥ አውቄአለሁ፥ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፥ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል።” 20#ዕብ. 11፥21።ስለዚህ በዚያን ቀን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “እስራኤላውያን በሚመርቁበት ጊዜ የእናንተን ስም በማስታወስ፥ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ’ ይላሉ።” 21እስራኤልም ዮሴፍን፦ “እነሆ እኔ እሞታለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፥ 22እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወስድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ” አለው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 48: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ