ኦሪት ዘፍጥረት 50
50
የያዕቆብ ቀብር
1ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም። 2ዮሴፍም አገልጋዮቹ የሆኑትን መድኃኒት ቀማሚዎች የአባቱን ሬሳ መልካም መዓዛ ባለው ሽቶ እያሹ እንዲያደርቁት ትእዛዝ ሰጠ። 3መድኃኒት ቀማሚዎቹም በሀገሩ ልማድ መሠረት ሬሳውን ለማድረቅ አርባ ቀን ፈጀባቸው። ግብጻውያን ሰባ ቀን ሙሉ አለቀሱለት።
4የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደሆን ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ 5#ዘፍ. 47፥29-31።አባቴ፦ ‘እነሆ እኔ እሞታለሁ፥ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ’ ሲል አስምሎኛል። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።” 6ፈርዖንም፦ “ሂድ፥ አባትህን እንዳስማለህ ቅበረው” አለው። 7ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፥ የፈርዖን አገልጋዮቹም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችና የግብጽ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፥ 8የዮሴፍም ቤተሰቦች ሁሉ፥ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተሰቦች ወጡ፥ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ። 9ሰረጎሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ። 10በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፥ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት። 11በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ፦ “ይህ ለግብጽ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፥” ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፥ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው። 12ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፥ 13#የሐዋ. 7፥16።ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፥ እርሷም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት። 14ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብጽ ተመለሱ።
ከያዕቆብ ሞት እስከ ዮሴፍ ሞት
15የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ፦ “ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።” 16ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት፦ “አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል፦ 17ዮሴፍን እንዲህ በሉት፦ ‘እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፥ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባርያዎች የበደሉህን ይቅር በል።’” 18ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው፦ “እነሆ እኛ ለአንተ ባርያዎችህ ነን አሉት።” 19ዮሴፍም አላቸው፦ “አይዞአችሁ አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ምትክ የምሆን ነኝ? 20እናንተ ክፋ ነገርን አሰባችሁብኝ፥ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው። 21አሁንም አትፍሩ፥ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ።” አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም።
22ዮሴፍ ከአባቱ ቤተሰቦች ጋር በግብጽ ተቀመጠ፤ ዮሴፍም መቶ ዐሥር ዓመት ኖረ። 23የኤፍሬምንም ልጆችና የልጅ ልጆች እስከሚያይ ድረስ ቈየ፤ ከምናሴ የተወለደውንም የማኪርንም ልጆች እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበላቸው። 24ዮሴፍም ወንድሞቹን፦ “እኔ እሞታለሁ፥ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል” አላቸው። 25#ዘፀ. 13፥19፤ ኢያ. 24፥32፤ ዕብ. 11፥22።ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች፦ “እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ” አስማላቸው። 26ዮሴፍም ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሞላው ሞተ፤ በሽቶም አሹት፥ በግብጽ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 50: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ