የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 11

11
እስራኤል ባያመሰግንም እንኳ ጌታ ምሕረትን ማድረጉ
1 # ዘፀ. 4፥22፤ ማቴ. 2፥15። እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። 2አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከእኔ ዘንድ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠው ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። 3እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ መራመድን አስተማርሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። 4ሰብአዊ በሆነ የርኅራኄ ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ እነርሱንም ጐንበስ ብዬ መገብኳቸው።
5ወደ እኔ መመለስን አልወደዱምና ወደ ግብጽ ምድር ይመለሳሉ፥ አሦርም ንጉሣቸው ይሆናል። 6ከመከሩትም ምክር የተነሣ ሰይፍ ከተሞቻቸውን ይመታል፥ ምዋርተኞቻቸውንም ይበላል ያጠፋልም። 7ሕዝቤም ከእኔ ወደ ኋላ መመለስን በጽኑ ወደዱ፤ በአንድነትም ወደ ልዑሉ ይጣራሉ፥ እርሱ ግን ከፍ ከፍ አያደርጋቸውም።
8 # ዘዳ. 29፥23። ኤፍሬም ሆይ! እንዴት እጥልሃለሁ? እስራኤል ሆይ! እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? እንዴትስ እንደ አድማህ አደርግሃለሁ? እንዴትስ እንደ ጲቦይም እመለከትሃለሁ? ልቤ በውስጤ ተናውጣለች፥ ምሕረቴም ተነሣሥታለች። 9እኔ አምላክ ነኝ እንጂ ሰው አይደለሁምና፥ በመካከልህም ቅዱሱ ነኝና የቁጣዬን መቅሠፍት አላደርግም፥ ኤፍሬምንም ዳግመኛ አላጠፋም፤ በመዓትም አልመጣም። 10ጌታን ይከተላሉ፥ እርሱም እንደ አንበሳ ያገሣል፤ ባገሣም ጊዜ ልጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከምዕራብ ይመጣሉ። 11እንደ ወፍም ከግብጽ፥ እንደ ርግብም ከአሦር ምድር እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በቤታቸውም አኖራቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ