የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሆሴዕ 2

2
የእስራኤል መታደስ
1የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንዳማይቆጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲሁም እነርሱ፦ “ሕዝቤ አይደላችሁም” በተባሉበት በዚያ ስፍራ፦ “የሕያው አምላክ ልጆች” ይባላሉ። 2የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ እነርሱም አንድ አለቃ በራሳቸው ላይ ይሾማሉ፤ የኢይዝራኤልም ቀን ታላቅ ይሆናልና ከምድሪቱ ይወጣሉ። 3ወንድሞቻችሁን፦ “ዓሚ”፥ እኅቶቻችሁንም፦ “ሩሃማ” በሉአቸው።
የእስራኤል አለመታመን፥ መቀጣትና መዳን
4እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባሏ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ምንዝርናዋን ከፊትዋ፥ ዝሙትዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤ 5አለበለዚያ ዕራቁትዋን እንድትሆን እገፍፋታለሁ፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር አደርጋታለሁ፥ በጥምም እገድላታለሁ። 6እንዲሁም የአመንዝራ ልጆች ናቸውና ለልጆችዋ አልራራም። 7እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም እርሷ አሳፋሪ ነገር አድርጋለች፤ ምክንያቱም፦ እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ፥ ብላለችና። 8ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፤ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ። 9ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለችም፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርሷም፦ ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና፥ ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ፥ ትላለች።
10እርሷም እህልንና ወይን ጠጅን ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም ያደረጉትን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደሆንኩ አላወቀችም። 11ስለዚህ እህሌን በጊዜው፥ ወይን ጠጄንም በወቅቱ ፈጽሞ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም መሸፈኛ የነበረውን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ። 12እንዲሁም አሁን ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም። 13ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችዋን ሁሉ አስቀራለሁ። 14እርሷም፦ “ውሽሞቼ ለእኔ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው” ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል። 15#ኢያ. 7፥24-26።በበኣሊም የበዓል ቀኖች ዕጣን ለእነርሱ በማጠንዋና ራስዋን በጉትቾችዋና በጌጥዋ በማስጌጥ ውሽሞችዋን ተከትላ እኔን በመርሳትዋ እቀጣታለሁ፥ ይላል ጌታ።
16ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ። 17ከዚያም የወይን ቦታዎችዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆናት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ብላቴንነትዋ ወራት ትዘምራለች። 18“በዚያ ቀን፦ ‘ባሌ’ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ፦ ‘በኣሌ’#2፥18 የጣኦት ስም። ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል ጌታ፤ 19የበኣሊምን ስም ከአፏ አስወግዳለሁና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በስማቸው የሚያስታውሳቸው አይኖርም። 20በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ጦርነትንም ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ በደኅንነትም እንዲያርፉ አደርጋቸዋለሁ። 21ለዘለዓለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ፥ በምሕረትና በጽኑ ፍቅር ለእኔ አጭሻለሁ። 22ለእኔም እንድትሆኚ በታማኝነት አጭሻለሁ፤ አንቺም ጌታን ታውቂአለሽ።
23 # ሮሜ 9፥25፤ 1ጴጥ. 2፥10። “እንዲህም ይሆናል፥ በዚያን ቀን እመልሳለሁ ይላል ጌታ፥ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤ 24ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ። 25በምድርም ላይ ለራሴ እንድትሆን እዘራታለሁ፤ ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፥ ሕዝቤም ያልሆነውን፦ ‘አንተ ሕዝቤ ነህ’ እለዋለሁ፤ እርሱም፦ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ ይለኛል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ