የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 17

17
1 # ኤር. 49፥23-27፤ አሞጽ 1፥3-5፤ ዘካ. 9፥1። ስለ ደማስቆ የተነገረ ትንቢት።
እነሆ፥ ደማስቆ ከተማነቷ ይቀራል፤ የፍርስራሽም ክምር ትሆናለች። 2ከተሞችዋ ለዘለዓለም ባድማ ይሆናሉ፤ ለመንጋ ማሰማርያ ይሆናሉ፤ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም። 3ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ይወገዳል፤ የሶርያም ትሩፍ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል፤ ይላል የሠራዊት ጌታ። 4በዚያን ቀን የያዕቆብ ክብር ይደበዝዛል፥ የሰውነቱም ውፍረት ይመነምናል። 5አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ፥ በራፋይም ሸለቆ እንደሚለቀም ቃርሚያ ይሆናል። 6የወይራ ዛፍ ሲያራግፉት በቅርንጫፉ ራስ ላይ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት ፍሬ ችፍግ ባለው ቅርንጫፍ ላይ እንደሚገኝ፥ እንዲሁ ጥቂት ቃርሚያ ይቀራል፥ ይላል ጌታ የእስራኤል አምላክ። 7በዚያ ቀን ሰዎች ወደ ፈጣሪያቸው ይመለከታሉ፤ ዐይኖቻቸውም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ። 8በእጃቸውም ወደ ሠሯቸው መሠዊያዎች አይመለከቱም፤ በጣቶቻቸው ወዳበጇቸው የዕጣን መሠዊያዎች ወይም ወደ ማምለኪያ ዐምዶች አይመለከቱም። 9በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ምክንያት የአሞራውያንና የኤዊያውያን ከተሞች ምድረ በዳ እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ጠንካራ ከተሞችህ ባድማም ይሆናሉ። 10አዳኝ አምላክህን ረስተሃል፤ መሸሸጊያ ዐለትህንም አላሰብክም፤ ስለዚህ ያማረውን ተክል ብትተክልም እንግዳንም ዘር ብትዘራ፥ 11በተከልክበት ቀን እንዲበቅል፥ በዘራህበት ማግስት እንዲያብብ ብታደርግ እንኳን፥ ነገር ግን በኀዘንና በብርቱ ደዌ ቀን መከሩ እንዳልነበር ይሆናል። 12እንደ ባሕር ሞገድ ለሚተም የብዙ ሕዝቦች ጩኸት፥ እንደ ኃያል የውኃ ሞገድ የሚያስገመግም ድምጽ ለሚያሰሙ ሕዝቦች ወዮላቸው! 13ሕዝቦች እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፤ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፤ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረውም ትቢያ ይበተናሉ። 14በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሽብር አለ! ከመንጋቱም በፊት አንዳቸውም አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙንም ዕጣ ይህ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ