ትንቢተ ኢሳይያስ 24
24
1እነሆ፥ ጌታ ምድርን ባዶ ያደርጋታል፥ ባድማም ያደርጋታል፥ ይገለብጣትማል፥ ነዋሪዎቿንም ይበትናል። 2በሕዝቡ ላይ የሚሆነው እንዲሁ ካህኑ ላይ ይሆናል፤ በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው እንዲሁ በአስተዳዳሪው፥ በአገልጋይቱም የሚሆነው እንዲሁ በእመቤትዋ፥ በሸማቹ ላይ የሚሆነው እንዲሁ በሻጩ፥ በአበዳሪው የሚሆነው እንዲሁ በተበዳሪው፥ በዕዳ አስከፋዩም የሚሆነው እንዲሁ በዕዳ ከፋዩ ይሆናል። 3ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ ፈጽማም ትበላሻለች፤ ጌታ ይህን ቃል ተናግሮአል።
4ምድርም አለቀሰች ረገፈችም፤ ዓለም ደከመች ረገፈችም፤ የምድርም ታላላቅ ሕዝቦች ዛሉ። 5ምድርም በነዋሪዎቿ ረክሳለች፥ ሕጉን ተላልፈዋልና፥ ሥርዓቱንም ለውጠዋልና፥ የዘለዓለሙንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል። 6ስለዚህ መርገም ምድርን ትበላለች፥ ነዋሪዎቿም ስለ ጥፋታቸው ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ይቃጠላሉ ጥቂት ሰዎችም ይቀራሉ። 7የወይን ጠጅ አለቀሰች፥ የወይን ግንድ ደከመች፥ ልባቸው ደስ ያለው ሁሉ ተከዙ። 8የከበሮው ሐሤት ቀርቷል፥ የደስተኞች ድምጽ ዝም ብሏል፥ የመሰንቆ ደስታ ቀርቶአል። 9እየዘፈኑም የወይን ጠጅን አይጠጡትም፥ የሚያሰክር መጠጥ የሚጠጡት መራራ ይሆንባቸዋል። 10ባድማ የሆነችው ከተማ ፈረሰች፤ ማንም እንዳይገባበት የሁሉም ቤት ተዘጋ። 11ስለ ወይኑም ጠጅ በአደባባይ ጩኸት ይሆናል፤ ደስታ ሁሉ ጨልሞአል፥ የምድርም ሐሤት ፈርሶአል። 12ከተማይቱም ባድማ ሆናለች፥ በርዋም በፍርስራሽ ተለውጧል። 13የወይራን ዛፍ እንደ መምታት፥ ከወይንም መከር በኋላ ቃርሚያውን እንደ መልቀም፥ እንዲሁ በምድርና በአሕዛብም መካከል ይሆናል።
14እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ እልልም ይላሉ፥ ስለ ጌታ ክብርም ከባሕር ይጣራሉ። 15ስለዚህ ጌታን በምሥራቅ፥ የእስራኤልንም አምላክ የጌታንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ። 16ለጻድቁ ክብር ይሁን የሚለውን ዝማሬ ከምድር ዳርቻ ሰምተናል። እኔ ግን፦ ከሳሁ፥ ከሳሁ፥ ወዮልኝ! ከሀዲዎች ክህደትን ፈጽመዋል፤ ከሀዲዎች አስከፊ ክህደት ፈጽመዋል አልሁ። 17በምድር ላይ የምትኖር ሆይ፥ ፍርሃትና ገደል ወጥመድም በአንተ ላይ አሉ። 18የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፥ የምድርም መሠረት ተናውጣለችና፥ ከሽብር ድምጽ የሸሸ በገደል ይወድቃል፥ ከገደልም የወጣ በወጥመድ ይያዛል። 19ምድር ተሰባበረች፥ ምድር ፈጽማ ደቀቀች፥ ምድር ተነዋወጠች። 20ምድር እንደ ሰካራም ትንገዳገዳለች፥ እንደ ዳስም ትወዛወዛለች፤ መተላለፍዋ ከብዷታል፥ ትወድቃለች፥ ደግማም አትነሣም። 21በዚያም ቀን እንደዚህ ይሆናል፤ ጌታ በከፍታ ያለውን ሠራዊት በከፍታ ላይ፥ በምድርም ያሉትን ነገሥታት በምድር ላይ ይቀጣቸዋል። 22በጉድጓድ እንደሚከማቹ እስረኞች በአንድነት ይከማቻሉ፤ በግዞት ቤትም ውስጥ ተዘግተው ይኖራሉ፥ ከብዙ ቀንም በኋላ ይቀጣሉ። 23የሠራዊት ጌታም በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚነግሥ በሽማግሌዎቹ ፊት ክብር ይሆናል፤ ጨረቃ ይታወካል ፀሐይም ያፍራል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 24: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ