ትንቢተ ኢሳይያስ 30
30
1ለዓመፀኞች ልጆች ወዮላቸው! ይላል ጌታ፤ ከእኔ ዘንድ ያልሆነን ምክር ይመክራሉ፥ ኃጢአትንም በኃጢአት ላይ ለመጨመር ከመንፈሴ ያልሆነውን ቃል ኪዳን ያደርጋሉ። 2ከአፌ ነገርን ሳይጠይቁ በፈርዖን ኃይል ለመጽናት በግብጽም ጥላ ለመታመን ወደ ግብጽ ይወርዳሉ። 3ስለዚህ የፈርዖን ኃይል እፍረት፥ በግብጽም ጥላ መታመን ስድብ ይሆንባቸዋል። 4አለቆች ምንም በጣኔዎስ ቢሆኑ፥ መልእክተኞችም ምንም ወደ ሐኔስ ቢደርሱ፥ 5ሁሉም ስለማይጠቅሟቸው፥ እፍረትና ስድብ እንጂ ረድኤትና ረብ ስለማይሆኗቸው ሕዝቡ ያፍራሉ። 6በደቡብ ስላሉ እንስሶች የተነገረ ራእይ። ተባትና እንስት፥ አንበሳ እፉኝትም፥ ተወርዋሪ እባብም በሚወጡባት፥ በመከራና በጭንቀት ምድር በኩል፥ ብልጥግናቸውን በአህዮች ጫንቃ ላይ፥ መዛግብቶቻቸውንም በግመሎች ሻኛ ላይ እየጫኑ ወደማይጠቅሟቸው ሕዝብ ይሄዳሉ። 7የግብጽ እርዳታ ከንቱና ምንም ነው፤ ስለዚህ ስሙን፦ “በቤት የሚቀመጥ ረዓብ” ብዬ ጠርቼዋለሁ። 8አሁንም ሂድ፥ ለሚመጣውም ዘመን ለዘለዓለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው። 9ዓመጸኛ ወገንና የጌታን ሕግ ለመስማት የማይወድዱ የሐሰት ልጆች ናቸውና፤ 10ባለ ራእዮችን፦ “አትመልከቱ” ይላሉ፥ ነቢያትንም፦ “ጣፋጩንና አታላዩን ነገር እንጂ ቅኑን ነገር አትንገሩን፤ 11ከመንገድ ፈቀቅ በሉ፥ ከጐዳናውም ዘወር በሉ፥ የእስራኤልንም ቅዱስ ከእኛ ዘንድ አስወግዱ” ይሏቸዋል። 12ስለዚህ የእስራኤል ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ይህችን ቃል አቃልላችኋልና፥ በግፍና በጠማምነት ታምናችኋልና፥ በእርሱም ተደግፋችኋልና፥ 13ስለዚህ ይህ በደል አዘብዝቦ ለመፍረስ እንደ ቀረበ፥ አፈራረሱም ፈጥኖ ድንገት እንደሚመጣ እንደ ረጅም ቅጥር ይሆንባችኋል። 14የሸክለኛ ማድጋ እንደሚሰበር ይሰብረዋል፥ ሳይራራም ያደቀዋል፤ ከስባሪውም እሳት ከማንደጃ የሚወስዱበት፥ ወይም ውኃ ከጉድጓድ የሚቀዱበት ገል አይገኝም። 15የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ ኃይላችሁ በጸጥታና በመታመን ይሆናል፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ፥ 16ነገር ግን፦ “በፈረስ ላይ ተቀምጠን እንሸሻለን እንጂ እንዲህ አይሆንም” አላችሁ፥ ስለዚህም ትሸሻላችሁ፤ ደግሞም፦ “በፈጣን ፈረስ ላይ እንቀመጣለን” አላችሁ፥ ስለዚህም የሚያሳድዷችሁ ፈጣኖች ይሆናሉ። 17ከአንድ ሰው ዛቻ የተነሣ ሺህ ሰዎች ይሸሻሉ፤ እናንተም በተራራ ራስ ላይ እንዳለ ምሰሶ፥ በኮረብታም ላይ እንዳለ ምልክት ሆናችሁ እስክትቀሩ ድረስ፥ ከአምስት ሰዎች ዛቻ የተነሣ ትሸሻላችሁ። 18ጌታም የፍርድ አምላክ ነው፤ ስለ ሆነም ጌታ ይራራላችኋልና ይታገሣል፤ ሊምራችሁም ከፍ ከፍ ይላል፤ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁ ሁሉ ብፁዓን ናቸው። 19በኢየሩሳሌም ውስጥ በጽዮን የምትኖር ሕዝብ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ አታለቅስም፤ በጩኸትም ድምፅ ይራራልሃል፥ በሰማህም ጊዜ ይመልስልሃል። 20ጌታም የጭንቀትን እንጀራና የመከራን ውኃ ቢሰጥህም አስተማሪህ እንግዲህ ከአንተ አይሰወርም፤ ዐይኖችህ ግን አስተማሪህን ያያሉ፥ 21ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ “መንገዷ ይህች ናት በእርሷም ሂድ” የሚለውን ቃል ይሰማሉ። 22በብርም የተለበጡትን የተቀረጹትን ምስሎችህን፥ በወርቅም የተለበጡትን ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎችህን ታረክሳለህ፤ እንደ ርኩስም ነገር ትጥላቸዋለህ፦ “ከእኔ ራቁ!” ትላቸዋለህ። 23በምድርም ለተዘራው ዘርህ ዝናብ ይሰጣል፥ ከምድርም ፍሬ የሚወጣ እንጀራ ወፍራምና ብዙ ይሆናል። በዚያም ቀን ከብቶችህ በሰፊ መስክ ይሰማራሉ፤ 24መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ጨው ጨው የሚለውን ገፈራ ይበላሉ። 25በታላቅም እልቂት ቀን ግንቦች በወደቁ ጊዜ በረጅሙ ተራራ ሁሉ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ፥ ወንዞችና የውኃ ፈሳሾች ይወርዳሉ። 26ጌታም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ መቅሰፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል። 27እነሆ፥ የጌታ ስም ከሚነድ ቁጣ፥ ከሚንቦለቦልም ጢስ ጋር ከሩቅ ይመጣል፤ ከንፈሮቹም በቁጣ የተሞሉ ናቸው፥ ምላሱም እንደምትበላ እሳት ናት፤ 28እስትንፋሱም አሕዛብን በአጥፊ ወንፊት ሊነፋቸው እንደሚያጥለቀልቅ እስከ አንገትም እንደሚደርስ ወንዝ ነው፤ በሕዝብም መንጋጋ የሚያስት ልጓም ይሆናል። 29በሌሊት የተቀደሰ በዓል ስታከብሩ እንደምትዘምሩ ዝማሬ፥ ወደ ጌታም ተራራ ወደ እስራኤል ዐለት እንቢልታ ይዞ በእልልታ እንደሚወጣ ሰው የልብ ሐሴትን ያደርጋል። 30ጌታም ክቡር ድምፁን ያሰማል፥ የክንዱንም መውረድ በሚነድ ቁጣውና በምትበላ እሳት ነበልባል፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በበረዶ፥ ጠጠርም ይገልጣል። 31አሦርም በበትር ከመታው ከጌታ ድምፅ የተነሣ ይደነግጣል። 32ጌታ በላዩ የሚወርድበት የታዘዘበት የበትር ድብደባ ሁሉ በከበሮና በመሰንቆ የታጀበ ይሆናል፤ በጦርነትም ክንዱን አንሥቶ ይዋጋቸዋል። 33ከቀድሞም ጀምሮ የማቃጠያ ስፍራ ተዘጋጅታለች፤ ለንጉሥም ተበጅታለች፤ ጥልቅና ሰፊም አድርጎአታል፤ እሳትና ብዙ ማገዶ ተከምሮአል፤ የጌታም እስትንፋስ እንደ ዲን ፈሳሽ ያቃጥለዋል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 30: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ