ትንቢተ ኢሳይያስ 34
34
1እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፥ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና ሞላዋ፥ ዓለምና ከእርሷ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ። 2የጌታ ቁጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው። 3ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ። ሬሳቸውም ይከረፋል፤ ተራሮችም በደማቸው ይርሳሉ። 4#ማቴ. 24፥29፤ ማር. 13፥25፤ ሉቃ. 21፥26፤ ራእ. 6፥13፤14።የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይሟሽሻሉ፤ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፤ ሠራዊታቸው ሁሉ ከወይንና ከበለስ ላይ እንደሚረግፍ ቅጠል ይረግፋል። 5#ኢሳ. 63፥1-6፤ ኤር. 49፥7-22፤ ሕዝ. 25፥12-14፤ 35፥1-15፤ አሞጽ 1፥11-12፤ አብ. 1፥1-14፤ ሚል. 1፥2-5።ሰይፌ በሰማይ ሆና ጠጥታ በምትረካበት ጊዜ፥ እነሆ፥ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች። 6ጌታ መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና፥ የጌታ ሰይፍ በደም ትርሳለች፤ ስብ ትጠግባለች፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ኩላሊት ስብ ትወፍራለች። 7ጎሽ ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትርሳለች፥ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች። 8ጌታ የበቀል ቀን፥ ስለ ጽዮንም የሚሟገትበት ዓመት አለው። 9የኤዶሚያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፥ አፈርዋም ዲን ይሆናል፥ መሬትዋም የሚቃጠል ዝፍት ትሆናለች። 10#ራእ. 14፥11፤ 19፥3።በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፤ ጢስዋም ለዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘለዓለም ዓለም ማንም አያልፍባትም። 11ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጉጉትና ቁራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የመጥፋት ቱንቢ ይዘረጋባታል። 12መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፥ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምቴዎች ይሆናሉ። 13በአዳራሾችዋም እሾህ፥ በቅጥሮችዋም ሳማና አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጎን ሥፍራ ትሆናለች። 14የምድረ በዳም አራዊት ከጅቦች ጋር ይገናኛሉ፤ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያም ትኖራለች፤ ለእርሷም ማረፊያ ታገኛለች። 15በዚያም ጉጉት ጎጆ ሠርታ እንቁላልን ትጥላለች፥ ትቀፈቅፋለችም፤ ጫጩቶቿንም በክንፏ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች ጥንድ ጥንድ ሆነው ይሰበሰባሉ። 16በጌታ መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ የጌታ አፍ አዝዞአልና፥ መንፈሱ ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ጥንዱን የሚያጣ የለም። 17እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፥ እጁም ለክታ ከፈለችላቸው፤ ለዘለዓለም የእነርሱ ትሆናለች፥ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይኖሩባታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 34: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ