ትንቢተ ኢሳይያስ 38
38
1በዚያም ጊዜ ሕዝቅያስ ለሞት በሚያደርስ ህመም ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል” አለው። 2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ ጌታ ጸለየ፦ 3“ጌታ ሆይ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፥ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ።” ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።
4ከዚያም የጌታም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5“ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው፦ የአባትህ የዳዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ። 6አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ።
7“ጌታም የተናገረውን ነገር እንደሚፈጽመው ከጌታ ይህ ምልክት ይሆንልሃል። 8እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍራ ሰዓት መቁጠሪያ ላይ በደረጃዎች ያለውን ከፀሐይ ጋር የወረደውን ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላው የሰዓት ስፍራ ላይ በወረደበት ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ። 9የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ ከበሽታው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሑፍ ይህ ነው፦ 10እኔ፦ በሕይወት ዘመኔ እኩሌታ ከሕይወት ልለይ ይገባልን? በቀረው ዘመኔስ ወደ ሲኦል በሮች መግባት አለብኝን? አልኩ። 11ደግሞም፦ በሕያዋን ምድር ጌታን አላይም፤ በዓለምም የሚኖሩትን ሰዎች ከእንግዲህ አልመለከትም አልኩ። 12ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልኩት፤ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ፍጻሜዬን አቀረብከው። 13እስኪ ነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ፍጻሜዬን አቀረብከው። 14እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጉረመረምሁ፤ ዐይኖቼ ወደ ላይ በማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ። 15ግን ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ።
16“ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስከኝ ወደ ሕይወትም መለስከኝ። 17እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ምክንያት ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጉድጓድ አዳንካት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ። 18#ሲራ. 17፥27፤ ባሮክ 2፥17።ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጉድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም። 19እኔ ዛሬ እንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆቹ እውነትህን ያስታውቃል። 20ጌታ ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።”
21ኢሳይያስም፦ “የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፥ እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር። 22ሕዝቅያስም፦ “ወደ ጌታ ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድነው?” ብሎ ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 38: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ