የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 5

5
ስለ ወይን ቦታ የተነገረ ቅኔ
1 # ማቴ. 21፥33፤ ማር. 12፥1፤ ሉቃ. 20፥9። ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤ ስለ ወዳጄ፤ ወዳጄ በለምለም ኮረብታ ላይ 2መሬቱን ቈፈረ፤ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤ ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት። በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤ የወይን መጭመቂያ ጉድጓድም አበጀ፤ ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ አሰበ፤ ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ። 3“እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤ በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ። 4ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር? መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ? 5እንግዲህ በወይኔ ቦታ ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤ ዐጥሩን እነቅላለሁ፤ ለጥፋት ይጋለጣል፤ ግንቡንም አፈርሳለሁ፤ መረጋገጫም ይሆናል። 6የማይኰተኰትና የማይታረም ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤ ኩርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤ ዝናብም እንዳይዘንብበት ደመናዎችን አዝዛለሁ።” 7የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የወይን ቦታ የእስራኤል ቤት ነው፤ የይሁዳ ሰዎችም የደስታው አትክልት ናቸው። ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤ ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።
ፍትህ አልባነትና ፍርድ
8ምንም ስፍራ ለሌሎች እስከማይተርፍ ድረስ፤ ቤትን በቤት ላይ በመጨመር፤ መሬትን ከመሬት ጋር በማያያዝ፤ ለብቻችሁ በምድር ተስፋፍታችሁ ለምትኖሩ ወዮላችሁ! 9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ታላላቅ ቤቶች ወና ይቀራሉ፤ የሚያማምሩም ቤቶች ነዋሪ ያጣሉ። 10ከሩብ ጋሻ የወይን ቦታ አንድ የባዶስ መስፈሪያ ያህል የወይን ጭማቂ ብቻ ይገኛል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር ተዘርቶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ብቻ ይሰጣል። 11#ጥበ. 2፥7-9።የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ ማልደው ለሚነሡ፤ እስኪያነዳቸውም ወይን በመጠጣት ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸው! 12በግብዣቸው ላይ በገናና መሰንቆ፤ ከበሮና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤ ነገር ግን ለጌታ ሥራ ቦታ አልሰጡም፤ ለእጆቹም ሥራ ክብር አላሳዩም። 13ስለዚህ ሕዝቤ ዕውቀት በማጣቱ ይማረካል፤ መኳንንቱም በራብ ይሞታሉ፤ ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል። 14ስለዚህ ሲኦል ሆዷን አሰፋች፤ አፏንም ያለ ልክ ከፈተች፤ መኳንንቱና ሕዝቡ ከረብሸኞቻቸውና ከጨፋሪዎቻቸው ጋር ወደዚያ ይወርዳሉ። 15ሰውም ዝቅ ዝቅ ይላል፤ ሰው ይዋረዳል፤ የእብሪተኛውም ዐይን ይሰበራል። 16የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍትሕ ከፍ ከፍ ይላል፤ ቅዱሱም አምላክ ቅድስናውን በጽድቅ ይገልጻል። 17በጎችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደሚሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤ የበግ ጠቦቶችም በባለጠጎች ፍርስራሽ ላይ ሣር ይበላሉ። 18ኃጢአትን በማታለል ገመድ ለሚስቡ፤ በደልንም በሠረገላ ማሰሪያ ለሚጐትቱ ወዮላቸው! 19በዐይናችን እንድናይ እግዚአብሔር ይቸኩል፤ ሥራውንም ያፋጥን፤ የእስራኤልን ቅዱስ፤ የእርሱን ዕቅድ እንድናውቃት ትቅረብ፤ ትምጣም ለሚሉ ወዮላቸው!” 20ክፉውን መልካም፤ መልካሙን ክፉ ለሚሉ ብርሃኑን ጨለማ፤ ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ፤ ጣፋጩን መራራ፤ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው! 21ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፤ በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው! 22የወይን ጠጅ ለመጠጣት ጀግኖች፤ የሚያሰክር መጠጥ ለመደባለቅ ብርቱ ለሆኑ ወዮላቸው! 23ጉቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፤ ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው! 24ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፤ ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፤ የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤ የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃለዋል። 25የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነዶአል፤ እጁን አንሥቶ መቶአቸዋል፤ ተራሮች ራዱ፤ ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደ ተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቁጣው ገና አልተመለሰም፤ እጁም እንደ ተነሣ ነው። 26ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትን ምልክት ያቆማል፤ ከምድር ዳርቻም በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ። 27በመካከላቸው ደካማና ስንኩል አይገኝም፤ የሚያንቀላፋና የሚተኛ አይኖርም፤ የወገባቸው መቀነት አይላላም፤ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም። 28ፍላጻቸው የተሳለ፤ ቀስታቸውም የተደገነ ነው፤ የሠረገሎቻቸውም መንኮራኩሮች እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው። 29ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤ እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤ ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤ ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም። 30በዚያን ቀን እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤ ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፥ ጨለማንና መከራን ያያል፤ ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ