ትንቢተ ኢሳይያስ 56
56
ለሚታዘዙት ሁሉ የተሰጠ ተስፋ
1ጌታ እንዲህ ይላል፦ ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ፤ ጽድቅንም አድረጉ። 2ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንንም የሚይዝ የሰው ልጅ፥ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው። 3ወደ ጌታም የተጠጋ መጻተኛ፦ “በእውነት ጌታ ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤ ጃንደረባም፦ “እነሆ፥ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል። 4#ጥበ. 3፥14፤15።ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰንበቴን ለሚጠብቁ፥ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ለሚመርጡ፥ ቃል ኪዳኔንም ለሚይዙ ጃንደረቦች፥ 5በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ሁሉ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ። 6ያገለግሉት ዘንድ የጌታንም ስም ለመውደድ አገልጋዮቹም ለመሆን ወደ ጌታ የሚጠጉትንም መጻተኞች፥ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን፥ በቃል ኪዳኔኔም የሚጸኑትን ሁሉ፥ 7#ማቴ. 21፥13፤ ማር. 11፥17፤ ሉቃ. 19፥46።ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ። 8ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር፦ ወደ ተሰበሰቡት ዘንድ ሌሎችን እሰበስብለታለሁ ይላል። 9እናንተ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ፥ እናንተም የዱር አራዊት ሁሉ፥ ትበሉ ዘንድ ቅረቡ። 10ጉበኞቹ ዕውሮች ናቸው፥ ሁሉም እውቀት የላቸውም፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው፤ መጮኽ አይችሉም፤ ሕልምን ያልማሉ፤ ይተኛሉ፤ እንቅልፍ ይወድዳሉ። 11መብል የሚወዱ ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው፤ እረኞቹም ማስተዋል የማይችሉ ናቸው፤ ሁሉም ወደ መንገዳቸው ዞሩ፥ ከፊተኛው እስከ ኋለኛው ድረስ ሁሉ፥ እያንዳንዳቸው ወደ ጥቅማቸው ዘወር ብለዋል። 12“ኑ የወይን ጠጅ እንውሰድ፥ በሚያሰክርም መጠጥ እንርካ፤ ዛሬም እንደሆነ እንዲሁ ነገ ይሆናል፥ ከዛሬም ይልቅ እጅግ ይበልጣል” ይላሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 56: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ