ትንቢተ ኢሳይያስ 60
60
የተበተኑት መሰብሰብ
1ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የጌታም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ። 2እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ ጌታ ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ 3አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ፥ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ። 4#ባሮክ 5፥5፤6።ዐይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሟቸዋል። 5በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጽግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል። 6የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ከከሳባ የሆኑት ሁሉ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፥ የጌታን ምስጋና ያወራሉ። 7የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ። 8ርግቦች ወደ ጎጇቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው? 9እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለጌታ ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ፥ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ለማምጣት፥ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል። 10በቁጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና ባዕዳን ቅጥርሽን ይሠራሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል። 11#ራእ. 21፥25-26።በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጽግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ለማምጣት ሌሊትና ቀን አይዘጉም። 12ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ። 13የመቅደሴንም ስፍራ ለማስጌጥ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው፥ ባርሰነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ። 14#ራእ. 3፥9።የአስጨናቂዎችሽ ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የጌታም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል። 15ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘለዓለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ። 16የአሕዛብንም ወተት ትጠጫልሽ፥ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም ጌታ፥ የያዕቆብ ኃያል፥ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደሆንሁ ታውቂያለሽ። 17በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፥ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ፤ 18ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ።
19 #
ራእ. 21፥23፤ 22፥5። ከዚያ በኋላ ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽም ይሆናልና በቀን ብርሃንሽ ፀሐይ መሆኑ ይቀራል፤ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያስፈልግሽም። 20ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም፥ ጨረቃሽም አትገባም። 21ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እንድከብር የአታክልቴን ቡቃያ፥ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘለዓለም ይወርሳሉ። 22ታናሹ ለሺህ፥ የሁሉም ታናሹ ኃያል መንግሥት ይሆናል፤ እኔ ጌታ በዘመኑ ይህን በፍጥነት አደርገዋለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 60: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ