የያዕቆብ መልእክት 4
4
ከዓለም ክፋት መጠንቀቅ
1በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ ከሚዋጋው ከፍትወት ምኞት አይደለምን? 2ትመኛላችሁ፤ ነገር ግን አታገኙም፤ ስለዚህ ትገድላላችሁ። በብርቱም ትመኛላችሁ፤ ልታገኙም አትችሉም፤ ስለዚህ ትጣላላችሁ፤ ትዋጋላችሁ። ስለማትለምኑ የምትፈልጉትን አታገኙም። 3የምትለምኑትም ለፍትወታችሁ በማሰብ በክፉ ምኞት ስለሆነ፥ ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም። 4አመንዝሮች ሆይ! ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላትነት መሆኑን አታውቁምን? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። 5ወይስ “እርሱ በውስጣችን ያሳደረው መንፈስ አብዝቶ ይቀናል” በማለት መጽሐፍ የተናገረው በከንቱ ይመስላችኋልን? 6#ምሳ. 3፥34።ስለዚህ፥ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” እንደሚል፥ የሚሰጠው ጸጋ ግን ከሁሉም ይበልጣል። 7እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። 8ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። እናንተ ኀጢአተኞች! እጃችሁን አንጹ፤ እናንተ በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉ ልባችሁን አጥሩ። 9ተጨነቁ፤ እዘኑ፤ አልቅሱም። ሳቃችሁ ወደ ኀዘን፥ ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። 10በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ፥ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።
በሰው ላይ መፍረድ እንደማይገባ
11ወንድሞች ሆይ! እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ፤ ወንድሙን የሚወነጅልና በወንድሙም ላይ የሚፈርድ በሕግ ላይ ክፉ ይናገራል፤ በሕግም ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ ብትፈርድ ፈራጅ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። 12ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ሊያድንና ሊያጠፋ የሚችል ነው፤ ነገር ግን በባልንጀራህ ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?
ስለ ትምክሕት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
13 #
ምሳ. 27፥1። #
ጥበ. 2፥4፤ 5፥9-13። እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ ተመልከቱ፤ 14ነገ የሚሆነውን አታውቁም። ሕይወታችሁ ምንድነው? ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት አይደላችሁምን? 15ይልቁንም፥ “የጌታ ፈቃድ ቢሆን እንኖራለን፤ ይህን ወይም ያንን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16እናንተ ግን በእብሪታችሁ ትመካላችሁ፤ እንዲህ ያለው ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው። 17እንግዲህ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ እንዳለበት እያወቀ የማያደርግ ሰው ኃጢአት ያደርጋል።
Currently Selected:
የያዕቆብ መልእክት 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ