ትንቢተ ኤርምያስ 28

28
ሐናንያ ነቢዩ ኤርምያስን ተቃውሞ መሞቱ
1 # 2ነገ. 24፥18-20፤ 2ዜ.መ. 36፥11-13። በዚያም ዓመት፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ፥ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር፥ ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በጌታ ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 2“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፦ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ። 3የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የጌታን ቤት ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳለሁ፤ 4ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና፥ የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና፥ ይላል ጌታ።”
5ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በጌታ ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ለሐናንያ ተናገረ። 6ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፦ “አሜን፥ ጌታ እንዲህ ያድርግ፤ የጌታን ቤት ዕቃዎችና ምርኮውን ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ ጌታ የተናገርኸውን የትንቢት ቃላት ይፈጽም። 7ነገር ግን በጆሮህና በሕዝብ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ፤ 8ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ጦርነትና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ። 9ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ ጌታ በእውነት የላከው ነቢይ እንደሆነ ይታወቃል።”
10ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው። 11ሐናንያም በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲሁ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ።” ነቢዩም ኤርምያስ መንገዱን ሄደ።
12ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የጌታ ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13“ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፥ ነገር ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር ተክተሀል። 14የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እንዲያገለግሉት የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ያገለግሉታል፥ ሌላው ቀርቶ የምድረ በዳ አራዊትን ሰጥቼዋለሁ።’ ” 15ነቢዩም ኤርምያስ ነቢዩን ሐናንያን፦ “ሐናንያ ሆይ! ስማ፤ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ ጌታ አልላከህም። 16ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እነሆ፥ ከምድር ላይ አስወግድሃለሁ፤ በጌታ ላይ ዓመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ’ ” አለው። 17ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ