ትንቢተ ኤርምያስ 34
34
ሴዴቅያስ ተማርኮ እደሚሞት ትምቢት መነገሩ
1 #
2ነገ. 25፥1-11፤ 2ዜ.መ. 36፥17-21። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ፥ ከእጁም ግዛት በታች ያሉ የምድር መንግሥታት ሁሉ፥ አሕዛብም ሁሉ ኢየሩሳሌምንና ከተሞችዋን ሁሉ ይወጉ በነበረ ጊዜ፥ ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2“የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሂድ ለይሁዳም ንጉሥ ለሴዴቅያስ ተናገር እንዲህም በለው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይህችን ከተማ በባቢሎን ንጉሥ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፥ በእሳትም ያቃጥላታል፤ 3አንተም በእርግጥ ትያዛለህ ለእጁም ተላልፈህ ትሰጣለህ እንጂ ከእጁ አታመልጥም፤ ዓይንህም የባቢሎንን ንጉሥ ዐይን ታያለች፥ እርሱም ከአንተ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገራል፥ ወደ ባቢሎንም ትሄዳለህ።’ 4ነገር ግን፥ የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሆይ! የጌታን ቃል ስማ፤ ጌታ ስለ አንተ እንዲህ ይላል፦ ‘በሰይፍ አትሞትም፤ 5በሰላም ትሞታለህ። ከአንተ በፊት እንደ ነበሩ እንደ ዱሮ ነገሥታት እንደ አባቶችህ ዕጣን እንደታጠነላቸው፥ እንዲሁ ለአንተም ዕጣንን ያጥኑልሃል፦ “ወየው! ጌታ ሆይ!” እያሉ ያለቅሱልሃል፤’ እኔ ቃልን ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ።”
6ነቢዩ ኤርምያስ እነዚህን ቃላት ሁሉ ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ነገረው፤ 7እንዲህም የተናገረው የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ የቀሩትን ለኪሶንና ዓዜቃንን በወጋ ጊዜ ነበር፤ ከተመሸጉት ከይሁዳ ከተሞች መካከል የተረፉት እነዚህ ብቻ ነበሩና።
በባሮች ላይ የሚደርስ የማታለል በደል
8ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። ይህም ቃል የመጣው ለባርያዎች ስለ አርነታቸው አዋጅ እንዲነገር ንጉሡ ሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም ከነበሩ ሕዝብ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን ካደረገ በኋላ ነው፤ 9አዋጁም፦ ሰው ሁሉ ዕብራዊ የሆነውን ወንድ ባርያውንና ዕብራዊት የሆነችውን ሴት ባርያውን አርነት እንዲያወጣ፥ አይሁዳዊ ወንድሙንም ማንም እንዳይገዛ የሚል ነው። 10ወደ ቃል ኪዳኑ የገቡ አለቆች ሁሉና ሕዝቡ ሁሉ ሰምተው ማንም ሰው ወንድ ባርያውንና ሴት ባርያውን አርነት እንዲያወጣ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ማንም እንዳይገዛቸው አደረጉ፤ እነርሱም ሰምተው አርነት አወጡአቸው። 11ነገር ግን ከዚያ በኋላ ተመልሰው አርነት ያወጡአቸውን ወንዶችና ሴቶች ባርያዎቻቸውን አስመለሱ፥ ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችም አድርገው ገዙአቸው። 12ስለዚህ የጌታ ቃል ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13“የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁን ከባርነት ቤት ከግብጽ አገር ባወጣኋቸው ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲህ ብዬ ቃል ኪዳን አደረግሁ፦ 14#ዘፀ. 21፥2፤ ዘዳ. 15፥12።‘ሰባት ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ የተሸጠላችሁን ስድስትም ዓመት ያገለገላችሁን ዕብራዊ ወንድማችሁን እያንዳንዳችሁ አርነት ታወጡታላችሁ፥ ለእናንተም ከሚሰጠው አገልግሎት ነጻ ታደርጉታላችሁ፤’ ነገር ግን አባቶቻችሁ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም። 15እናንተም ዛሬ ተመልሳችሁ፥ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን አርነት ለማውጣት አዋጅ በመንገር ለዓይኔ ደስ የሚያሰኝን ነገር አድርጋችሁ ነበር፥ ስሜም በተጠራበት ቤት ውስጥ በፊቴ ቃል ኪዳን አድርጋችሁ ነበር። 16ነገር ግን ተመልሳችሁ ስሜን አስነቀፋችሁ፥ እያንዳንዳችሁም በፈቃዳቸው እንዲሄዱ አርነት ያወጣችኋቸውን ወንድና ሴት ባርያዎቻችሁን አስመለሳችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችም እንዲሆኑላችሁ ገዛችኋቸው።
17“ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰው ሁሉ ለወንድሙና ለባልንጀራው የአርነት አዋጅ ለመንገር እኔን አልሰማችሁም፤ እነሆ፥ እኔ ለሰይፍና ለቸነፈር ለራብም የአርነት አዋጅ እናገርባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ በምድር መንግሥታትም ሁሉ ዘንድ ለድንጋጤ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ። 18ቃል ኪዳኔንም የተላለፉትን ሰዎች፥ እንቦሳውንም ቈርጠው በቁራጩ መካከል ባለፉ ጊዜ በፊቴ ያደረጉትን የቃል ኪዳኑን ሕግጋት ያልፈጸሙትን፥ 19የይሁዳን አለቆችና የኢየሩሳሌምን አለቆች እንዲሁም ጃንደረቦችንና ካህናትን በእንቦሳም ቁራጭ መካከል ያለፉትን የአገሩን ሕዝብ ሁሉ፥ 20ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሬሳቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል። 21የይሁዳንም ንጉሥ ሴዴቅያስንና አለቆቹን፥ ለጠላቶቻቸው እጅ ነፍሳቸውንም ለሚሹአት እጅ ከእናንተም ለተመለሱት ለባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ። 22እነሆ፥ አዝዛለሁ፥ ይላል ጌታ፥ ወደዚህችም ከተማ እመልሳቸዋለሁ፤ እርሷንም ይወጋሉ ይይዙአታልም በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የሌለበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 34: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ