የዮሐንስ ወንጌል 10:1-17

የዮሐንስ ወንጌል 10:1-17 መቅካእኤ

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች በረት በበሩ ሳይሆን የማይገባ በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ ሌባና ወንበዴ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች እረኛ ነው። ለእርሱ በር ጠባቂው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፤ የእራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የእራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፤ የሌሎቹን ድምፅ አያውቁምና።” ኢየሱስ ይህንን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን የነገራቸው ምን እንደሆነ አላስተዋሉም። ኢየሱስም ደግሞ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የበጎች በር ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፤ ዳሩ ግን በጎቹ አልሰሙአቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል፤ ይገባልም፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ለሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወትን እንዲያገኙ፥ የተትረፈረፈ ሕይወትን እንዲያገኙ መጣሁ፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑት ተቀጣሪው ግን፥ ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል፤ በጎቹንም ይበትናቸዋል። ተቀጣሪ ስለሆነ፥ ለበጎቹም ስለማይገደው ይሸሻል። መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ የእራሴን በጎች አውቃለሁ፤ የእራሴም በጎች ያውቁኛል። አብም እንደሚያውቀኝ፥ እኔም አብን እንደማውቀው፤ ነፍሴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱን ደግሞ ማምጣት ይገባኛል፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ አንድም መንጋ ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለመውሰድ ነፍሴን አሳልፌ ስለምሰጥ አብ ይወደኛል።