መጽሐፈ ኢዮብ 38
38
1እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“እውቀት በጎደለው ንግግር
ምክርን የሚያጨልመው ማነው?
3እንግዲህ እንደ ጎበዝ ወገብህን ታጠቅ፥
እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ታሳውቀኛለህ።
4ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ?
ታስተውል እንደሆንህ ተናገር።
5የምታውቅ እንደሆነ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥
በላይዋም የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?
6-7 #
ባሮክ 3፥34። አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥
የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥
መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር?
የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?
8 #
ኤር. 5፥22። ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ
ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው?
9ደመናውን ለልብሱ፥
ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፥
10ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥
መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦
11እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፥
በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ።
12በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘህ ታውቃለህን?
ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን?
13የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥
ከእርሷም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥
14ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁም እርሱ ይለወጣል፥
ፍጥረትም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል።
15ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥
ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል።
16ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገበተሃልን?
በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን?
17የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን?
የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን?
18ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን?
ሁሉን አውቀህ እንደሆነ ተናገር።
19-20ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥
ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥
የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው?
የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ?
21በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥
የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥
በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም።
22በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን?
የበረዶውንስ ቤተ መዛግብት አይተሃልን?
23ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለውጊያና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።
24ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፋፈላል?
የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል?
25-26ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥
27ሣሩንም እንዲያበቅል፥
ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥
ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብ እንዲዘንብ፥
ለፈሳሹ ውኃ መተላለፊያውን፥
ወይም ለሚያንጐደጉድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው?
28በውኑ ለዝናብ አባት አለውን?
ወይም የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?
29በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ?
የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው?
ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ 30የቀላዩም ፊት ረግቶአል።
31 #
ኢዮብ 9፥9፤ አሞጽ 5፥8። በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥
ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን?
32ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥
ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን?
33የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን?
በምድርስ ለይ እንዲፈጸም ማድረግ ትችላለህን?
34የውኆች ሙላት ይሸፍንህ ዘንድ።
ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን?
35መብረቆች ሄደው፦ ‘እነሆ፥ እዚህ አለን’ ይሉህ ዘንድ፥
ልትልካቸው ትችላለህን?
36በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥
ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?
37-38የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው?
ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥
ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥
የሰማይን ደመና ለዝናብ ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?
39-40በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥
በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥
ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን?
የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን?
41ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ
የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥
ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 38: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ