ኦሪት ዘሌዋውያን 26

26
ስለ መታዘዝ የሚሰጥ ሽልማት
1 # ዘሌ. 19፥4፤ ዘፀ. 20፥4፤ ዘዳ. 5፥8፤ 16፥21፤22፤ 27፥1። “እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝና ለራሳችሁ ይሆኑ ዘንድ ጣዖታትን አትሥሩ፥ የተቀረጸም ምስል ወይም ሐውልት አታቁሙ፤ ለእርሱም ለመስገድ በምድራችሁ ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ። 2ሰንበታቴን ጠብቁ፥ ለመቅደሴም ክብርን ስጡ፤ እኔ ጌታ ነኝ።
3 # ዘዳ. 11፥13-15፤ 28፥1-14። “በሥርዓቶቼ ብትመላለሱ፥ ትእዛዛቴንም ብትጠብቁ ብታደርጉአቸውም፥ 4ዝናባችሁን በወቅቱ አዘንባለሁ፥ ምድሪቱም የተትረፈረፈ ምርትዋን ትሰጣለች፥ የሜዳው ዛፎችም ፍሬአቸውን ይሰጣሉ። 5ለእናተም እህሉን ማበራየቱ የወይኑን ዘለላ እስከሚቆረጥበት ወቅት ድረስ ይደርሳል፥ የወይኑንም ዘለላ መቁረጥ እህል እስከ ሚዘራበት ወቅት ድረስ ይደርሳል፤ እስክትጠግቡም ድረስ እንጀራችሁን ትበላላችሁ፥ በምድራችሁም ላይ በደኅንነት ትቀመጣላችሁ። 6በምድሪቱም ላይ ሰላምን እሰጣለሁ፥ ማንም ሳያስፈራራችሁ ያለ ስጋት ትተኛላችሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፥ ሰይፍም በምድራችሁ ላይ አያልፍም። 7ጠላቶቻችሁንም ታሳድዳላችሁ፥ በእናንተም ፊት በሰይፍ ይወድቃሉ። 8ከእናንተም አምስቱ መቶውን ያሳድዳሉ፥ መቶውም ዓሥሩን ሺህ ያሳድዳሉ፤ ጠላቶቻችሁም በእናንተ ፊት በሰይፍ ይወድቃሉ። 9ወደ እናንተም ዘወር ብዬ በበጎ እመለከታችኋለሁ፥ እንድታፈሩም አደርጋችኋለሁ፥ አበዛችሁማለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም ከእናንተ ጋር አጸናለሁ። 10ለብዙም ጊዜ በጎተራ የተቀመጠውን ቀድሞ የነበረውን እህል ትበላላችሁ፤ ለአዲሱም ቦታ ለማስለቀቅ ቀድሞ በጎተራ የነበረውን ታወጣላችሁ። 11ማደሪያዬንም በእናንተ መካከል አደርጋለሁ፤ ነፍሴም አትጸየፋችሁም። 12#2ቆሮ. 6፥16።በመካከላችሁም እመላለሳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ። 13ባርያዎች እዳትሆኑአቸው ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ የባርነታችሁን ቀንበር ሰብሬአለሁ፤ ቀና ብላችሁም እንድትሄዱ አድርጌአችኋለሁ።”
አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት
14 # ዘዳ. 28፥15-68። ጌታም እንዲህ አለ፦ “ነገር ግን እኔን ባትሰሙና እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 15ሥርዓቴንም ባትቀበሉ፥ ነፍሳችሁም ፍርዴን በመጸየፉዋ ምክንያት ትእዛዛቴን ሳታደርጉ ቃል ኪዳኔን ብታፈርሱ፥ 16እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፤ ፍርሃትን፥ ነፍስን የሚያኮስስና ዓይንን የሚያፈዝዝ ክሳትና ትኩሳት አመጣባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ይበሉታልና ዘራችሁን በከንቱ ትዘራላችሁ። 17ፊቴንም አጠቊርባችኋለሁ፥ በጠላቶቻችሁም ፊት ትሸነፋላችሁ፤ የሚጠሉአችሁም ይገዙአችኋል፤ ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ። 18እነዚህም ነገሮች ተደርገውባችሁ እንኳ ባትሰሙኝ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ ጨምሬ ዳግመኛ እቀጣችኋለሁ። 19የኃይላችሁንም ትዕቢት እሰብራለሁ፤ ሰማያችሁንም እንደ ብረት፥ ምድራችሁንም እንደ ናስ አደርጋለሁ። 20ጉልበታችሁም በከንቱ ያልቃል፤ ምድራችሁም የተትረፈረፈውን ምርትዋን አትሰጥም፥ የምድሪቱም ዛፎች ፍሬያቸውን አይሰጡም።
21“እኔንም በመቃወም ብትሄዱ ልትሰሙኝም ባትፈልጉ፥ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ ቸነፈር እጨምርባችኋለሁ። 22በመካከላችሁም የዱር አራዊትን እለቅባችኋለሁ፤ ልጆቻችሁንም ይነጥቁአችኋል፥ እንሰሶቻችሁንም ያጠፉባችኋል፥ እናንተንም ቁጥራችሁን ያመነምኑታል፤ መንገዶቻችሁም የተራቈቱ ይሆናሉ።
23“በእነዚህም ተቀጥታችሁ ወደ እኔ ባትመለሱ፥ ይልቁንም እኔን በመቃወም ብትሄዱ፥ 24እኔም ደግሞ እናንተን በመቃወም እሄዳለሁ፤ እኔም ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 25የቃል ኪዳኑንም በቀል የሚበቀል ሰይፍ አመጣባችኋለሁ፤ ወደ ከተሞቻችሁም ትሰበሰባላችሁ፥ በመካከላችሁም ቸነፈርን እልክባችኋለሁ፤ በጠላትም እጅ ተላልፋችሁ ትሰጣላችሁ። 26የእንጀራችሁንም በትር በሰበርሁ ጊዜ፥ ዐሥር ሴቶች እንጀራችሁን በአንድ ምጣድ ይጋግራሉ፥ በሚዛንም መዝነው ዳግመኛ እንጀራችሁን ያመጡላችኋል፤ ትበላላችሁም ነገር ግን አትጠግቡም።
27“ይህም ተደርጎባችሁ እንኳ ባትሰሙኝ፥ እኔንም በመቃወም ብትሄዱ፥ 28እኔ ደግሞ በቁጣ እናንተን በመቃወም እሄዳለሁ፤ እኔም ስለ ኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29የወንዶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴቶች ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ። 30የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ፥ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ ሬሳችሁንም በጣዖቶቻችሁ ሬሳዎች ላይ እጥላለሁ፤ ነፍሴም ትጸየፋችኋለች። 31ከተሞቻችሁንም አፈርሳለሁ፥ መቅደሶቻችሁንም ባድማ አደርጋለሁ፥ መልካሙንም መዓዛችሁን አላሸትም። 32ምድሪቱንም የተራቈተች አደርጋለሁ፤ የሚቀመጡባትም ጠላቶቻችሁ በእርሷ ላይ ይሣቀቃሉ። 33እናንተንም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም ባድማ ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ይፈርሳሉ።
34“በዚያም በጠላቶቻችሁ ምድር ሳላችሁ፥ ምድሪቱ ባድማ ሆና እስከተቀመጠችበት ጊዜ ድረስ ሁሉ ሰንበታትን በማድረግዋ ትደሰታለች፤ በዚያም ጊዜ ምድሪቱ ታርፋለች፥ ሰንበታትንም በማድረግዋ ትደሰታለች። 35እናንተ ተቀምጣችሁባት በነበረ ጊዜ በሰንበቶቻችሁ ያልነበራትን እረፈት ባድማ ሆና እስከተቀመጠችበት ጊዜ ድረስ ሁሉ ይኖራታል። 36በጠላቶቻቸውም ምድሮች ሳሉ ከእናንተ መካከል በተረፉት ላይ በልባቸው ድንጋጤን እልክባቸዋለሁ፤ በነፋስም የምትንቀሳቀስ የቅጠል ድምፅ ታስደነብራቸዋለች፤ እነርሱም ከሰይፍ እንደሚሸሹ ይሸሻሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ። 37ማንም ሳያሳድዳቸው ከሰይፍ እንደሚሸሹ እርስ በርሳቸው ይሰነካከላሉ፤ እናንተም በጠላቶቻችሁ ፊት የምትቆሙበት ኃይል አይኖራችሁም። 38በአሕዛብም መካከል ታልቃላችሁ፥ የጠላቶቻችሁም ምድር ትውጣችኋለች። 39ከእናንተም መካከል የተረፉት በጠላቶቻቸው ምድር ላይ በኃጢአታቸው ይመነምናሉ፤ በአባቶቻቸውም ኃጢአት ደግሞ እንደ እነርሱ ይመነምናሉ።
40“ነገር ግን እኔን በመቃወም ሄደዋልና፥ በእኔ ላይ ፈጽሞ በከዳተኝነት ያደረጉትን በደላቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ይናዘዛሉ። 41እኔም ደግሞ እነርሱን በመቃወም እሄዳለሁ፤ ወደ ጠላቶቻቸውም ምድር አመጣቸዋለሁ፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ያልተገረዘው ልባቸው ቢዋረድ፥ የበደላቸውንም ቅጣት ቢቀበሉ፥ 42#ዘፍ. 28፥13፤14፤ ዘፍ. 26፥3፤4፤ ዘፍ. 17፥7፤8።እኔም ለያዕቆብ የማልሁትን ቃል ኪዳኔን አስታውሳለሁ፤ እንዲሁም ለይስሐቅና ለአብርሃም የማልሁትንም ቃል ኪዳኔን አስታውሳለሁ፤ ምድሪቱንም አስታውሳለሁ። 43ምድርሪቱም በእነርሱ ትተዋለች፤ ያለ እነርሱም ባድማ ሆና እስከተቀመጠችበት ጊዜ ድረስ ሰንበታትን በማድረግዋ ትደሰታለች፤ ፍርዴንም ስላልተቀበሉ፥ ነፍሳቸውም ሥርዓቴን ስለ ተጸየፈች የበደላቸውን ቅጣት ይቀበላሉ። 44በዚህ ነገር ሁሉ ግን እኔ ጌታ አምላካቸው ነኝና እነርሱ በጠላቶቻቸው ምድር ሳሉ፥ ፈጽሞ እስካጠፋቸው ድረስ ከእነርሱም ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን እስካፈርስ ድረስ አልጥላቸውም አልጸየፋቸውምም። 45እኔ አምላክ እንድሆናቸው አሕዛብ እያዩ ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ከአባቶቻቸው ጋር ያለኝን ቃል ኪዳን ስለ እነርሱ አስታውሳለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።”
46ጌታም በእርሱና በእስራኤል ልጆች መካከል በሲና ተራራ ላይ በሙሴ እጅ የሰጣቸው ሥርዓቶችና ፍርዶች ሕግጋትም እነዚህ ናቸው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ