የሉቃስ ወንጌል 24:1-53

የሉቃስ ወንጌል 24:1-53 መቅካእኤ

ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እጅግ ማልደው፥ ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ወደ መቃብሩ መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ወዲያ ተንከባሎ አገኙት፤ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን አስከሬን አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲገረሙ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው “ሕያዉን ለምን በሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እርሱ እዚህ የለም፤ ይልቁንም ተነሥቶአል። ገና በገሊላ እያለ የነገራችሁን አስታውሱ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ ተላልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው።” እነርሱም ቃሎቹንም አስታወሱ፤ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለዐሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። ይህንንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና፥ የያዕቆብም እናት ማርያም፥ እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የነበሩ ሌሎች ሴቶች ነበሩበት። ነገር ግን ይህ ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት ቀጭን የሐር ልብስ ለብቻ ተቀምጦ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ። እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ዐሥራ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዐይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም “አብራችሁ እየሄዳችሁ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሯቸው እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?” አላቸው። እነርሱም አዝነው ቀጥ ብለው ቆሙ። ቀለዮጳ የሚባለውም አንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት “በእነዚህ ቀኖች በኢየሩሳሌም የተከሠተውን ነገር የማታውቅ እንግዳ አንተ ብቻ ነህን?” እርሱም “ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ “በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ነው፤ የካህናት አለቆቻችንና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን የሚታደገው እርሱ ነው ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም ይህ ነገር ከሆነ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። አስከሬኑንም ባጡ ጊዜ ‘ሕያው ነው’ የሚሉ መላእክትን በራእይ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛ ጋር ከነበሩት አንዳንዶች ወደ መቃብር ሄደው ሴቶቹ እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፤ እርሱን ግን አላዩትም።” እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታስተውሉ፤ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት ይገባው የለምን?” ከዚህ በኋላ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን አብራራላቸው። ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፤ እርሱም አልፎ የሚሄድ መሰለ። እነርሱ ግን “እኛ ጋር እደር፤ እየመሸ ነው፥ ቀኑም እያለቀ ነውና፤” ሲሉ አጥብቀው ለመኑት፤ እርሱም እነርሱ ጋር ሊያድር ገባ። ከእነርሱም ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፤ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ዐይናቸውም ተከፈተና አወቁት፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። እርስ በርሳቸውም “በመንገድ ሳለን ሲያናግረንና መጻሕፍትንም ሲያስረዳን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ። በዚያችም ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዐሥራ አንዱንና ከእነርሱ ጋር የነበሩትንም በአንድነት ተሰብስበው አገኙአቸው። እነርሱም “ጌታ በእርግጥ ተነሥቷል፥ ለስምዖንም ታይቷል” ይሉ ነበር። እነርሱም በመንገድ የሆነውን፥ እንጀራውንም በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው። ይህንንም ሲነጋገሩ ሳለ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” አላቸው። እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሃት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው “ስለምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ያድራል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ ዳስሱኝና እዩ፥ መንፈስ በእኔ እንደምታዩት፥ ሥጋና አጥንት የለውምና፤” ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከደስታ ብዛት ገና ሳያምኑ ገና በመገረም ላይ ሳሉ “በዚህ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ትንሽ የተጠበሰ ዓሣ ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ። ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው “እንዲህ ተጽፏል፥ ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን እንደሚነሣ፤ በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ እንደሚሰበክ፤ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ። እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በዚህች ከተማ ቆዩ።” እስከ ቢታንያም ወሰዳቸው፤ እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። እየባረካቸውም ከእነርሱ ተለየ፤ ወደ ሰማይም ዐረገ። እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በመቅደስ ኖሩ።