የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማቴዎስ ወንጌል 11

11
ከመጥምቁ ዮሐንስ የተላኩ መልእክተኞች
(ሉቃ. 7፥17-35)
1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ በኋላ፥ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ሄደ።
2ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና 3“የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” አለው። 4ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ 5#ኢሳ. 35፥5፤6፤ ኢሳ. 61፥1።ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ 6በእኔ የማይሰናከል ሁሉ የተባረከ ነው።”
7እነርሱ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆ? 8ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። 9ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ነውን? አዎን፥ ከነቢይም የሚበልጠውን እላችኋለሁ።
10 # ሚል. 3፥1። “እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ
መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤” ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና።
11እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። 12#ሉቃ. 16፥16።ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም በኃይል ይወስዱአታል። 13ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና፤ 14#ሚል. 4፥5፤ ማቴ. 17፥10-13፤ ማር. 9፥11-13።ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ እርሱ ነው። 15የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
16“ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ ተቀምጠው እርስ በእርሳቸው እንዲህ እያሉ የሚጠሩ ልጆችን ይመስላሉ፤ 17‘ዋሽንት ነፋንላችሁ አልጨፈራችሁም፥ ሙሾ አወረድንላችሁ አላለቀሳችሁም’ ይሉአቸዋል። 18ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘ጋኔን አለበት’ አሉት። 19የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘እነሆ በላተኛና ጠጪ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ በሥራዋ ጸደቀች።”
ንስሓ ባለመግባታቸው የተወቀሱ ከተሞች
(ሉቃ. 10፥13-15)
20በዚያን ጊዜ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች ንስሓ ስላልገቡ ይነቅፋቸው ጀመር፤ 21#ኢሳ. 23፥1-18፤ ሕዝ. 26፥1—28፥26፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9፤10፤ ዘካ. 9፥2-4።“ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው፥ አመድ ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። 22ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። 23#ኢሳ. 14፥13-15፤ ዘፍ. 19፥24-28።አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በቆየች ነበር። 24#ማቴ. 10፥15፤ ሉቃ. 10፥12።ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል።”
25በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “የሰማያትና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። 26አዎን አባት ሆይ! ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። 27#ዮሐ. 3፥35፤ ዮሐ. 1፥18፤ 10፥15።ሁሉም ነገር በአባቴ ለእኔ ተሰጥቶአል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን የሚያውቅ የለም። 28#ሲራ. 6፥24-30፤ 24፥19፤ 51፥23-26።እናንተ ደካሞችና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። 29#ኤር. 6፥16።ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፥ ከእኔም ተማሩ፤ ምክንያቱም እኔ የዋህ በልብም ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ 30ቀንበሬ ልዝብ፥ ሸክሜም ቀላል ነውና።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ