የማቴዎስ ወንጌል 26:69-75

የማቴዎስ ወንጌል 26:69-75 መቅካእኤ

ጴጥሮስም ከቤት ውጪ በግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድ ወደ እርሱ ቀርባ “አንተም ከገሊላዊው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው። እርሱ ግን “የምትዪውን አላውቀውም” ብሎ በሁሉም ፊት ካደ። ሊወጣ ወደ በሩ ሲሄድ ሌላዪቱ አየችውና በዚያ ለነበሩት “ይህም ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ” አለቻቸው። “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ እየማለ ካደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያ ቆመው የነበሩት ጠጋ ብለው ጴጥሮስን “በእውነት አንተም ከእነርሱ ወገን ነህ፤ አነጋገርህ ያስታውቅብሃልና” አሉት። በዚያን ጊዜ “ሰውየውን አላውቀውም” ብሎ ይራገምና ይምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ጴጥሮስም “ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ የተናገረውን የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።