ትንቢተ ሚክያስ 6

6
እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ወቀሰ
1ጌታ የሚለውን ስሙ፥ ተነሥ፥ በተራሮች ፊት ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ኮረብቶች ቃልህን ይስሙ።
2ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ የጌታን ወቀሳ ስሙ፤ ጌታ ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይዋቀሳልና።
3ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አደረግሁህ? ያደከምኩህስ እንዴት ነው? መልስልኝ።
4 # ዘፀ. 12፥50፤51፤ ዘፀ. 4፥10-16፤ ዘፀ. 15፥20። ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁና፤ በፊትህም ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን ላክሁልህ።
5 # ዘኍ. 22፥2—24፥25፤ ኢያ. 3፥1—4፥19። ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ያቀደውን፥ የቤዖር ልጅ በለዓም የመለሰለትን፥ የጌታን ጽድቅ እንድታውቅ ከሺጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ የሆነውን እባክህን አስታውስ።
እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው ነገር
6ምን ይዤ ወደ ጌታ ፊት ልቅረብ፥ በልዑል አምላክ ፊት ልስገድን? የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድ ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልቅረብን?
7ጌታስ በእልፍ አውራ በጎች፥ በብዙ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? የበኩር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት ልስጠውን?
8ሰው ሆይ፥ መልካም ምን እንደሆነ ለአንተ ነግሮሃል፤ ፍትሕን እንድታደርግ፥ ምሕረትን እንድትወድና ከአምላክህም ጋር በትሕትና እንድትሄድ ካልሆነ በቀር ጌታ ከአንተ የሚፈልገው ምንድነው?
ማታለልና ዓመጽ እንደሚያስቀጣ
9የጌታ ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ ወገን ሆይ፥ ያዘጋጀው ማን እንደሆነ ስሙ።
10በክፉ ቤት የክፋት መዝገብ፥ አስጸያፊ ሐሰተኛ መስፈሪያ አሁንም አለን?
11የክፋት ሚዛንንና የአታላይ መመዘኛ ከረጢት አነጻለሁን?
12ባለ ጠጎችዋ ግፍ ተሞልተዋል፤ በውስጧ የሚኖሩትም ሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ አታላይ ነው።
13ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቁስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈረስሁህ።
14ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ባዶነትህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን ወደ ደህንነት አታመጣም፥ ወደ ደህንነት ያመጣኸውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ።
15ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራ ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይን ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም።
16 # 1ነገ. 16፥23-28፤ 1ነገ. 16፥29-34፤ 21፥25፤26። የዖምሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቀሃልና፥ በምክራቸውም ሄዳችኋልና፤ ስለዚህ አንተን ለጥፋት ነዋሪዎቿን ደግሞ ለመዘባበቻ ሰጥቻችኋለሁ፥ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ