የማርቆስ ወንጌል 4
4
የዘሪው ምሳሌ
(ማቴ. 13፥10-17፤ ሉቃ. 8፥4-8)
1 #
ሉቃ. 5፥1-3። እንደገናም በባሕር ዳርቻ ያስተምር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ እርሱ በባሕሩ ላይ በነበረች ጀልባ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ነበሩ። 2በምሳሌም ብዙ ነገር አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ 3“ስሙ! እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። 5ሌላውም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6ፀሐይም ሲወጣ ጠወለገ፤ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። 7ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው፤ ፍሬም አልሰጠም። 8ሌላውም በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ አደገ፤ አድጎም ፍሬ ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ስልሳ፥ አንዱም መቶ አፈራ።” 9ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ፤” አለ።
10ብቻውንም በሆነ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በዙሪያው የነበሩት ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 11እርሱም፥ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷአችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ 12#ኢሳ. 6፥9፤10።ይኸውም፦
ተመልሰው ይቅር እንዳይላቸው፥
‘ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤
መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’”
አላቸው። 13እንዲህም ሲል ጠየቃቸው፦ “ይህን ምሳሌ ያልተረዳችሁ፥ እንዴት ሌሎችን ምሳሌዎች ሁሉ ታውቃላችሁ? 14ዘሪው ቃሉን ይዘራል። 15ቃሉ በተዘራ ጊዜ በመንገድ ዳር የነበሩት፦ እነርሱ በሰሙት ጊዜ ሰይጣን ወዲያው መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል የሚወስድባቸው ናቸው። 16እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ 17ለጊዜው ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፤ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ። 18በእሾህም የተዘሩት ሌሎች ናቸው፤ ቃሉን የሰሙት እነዚህ ናቸው፤ 19የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቃሉን ያንቃሉ፤ የማያፈራም ይሆናል። 20በመልካምም መሬት የተዘሩት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉት አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ የሚያፈሩት እነዚህ ናቸው።”
መብራትን አብርተው ከዕንቅብ በታች እንደማያስቀምጡ
(ሉቃ. 8፥16-18)
21 #
ማቴ. 5፥15፤ ሉቃ. 11፥33። እንዲህም አላቸው “መብራትን ከዕንቅብ ወይስ ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን? በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን? 22#ማቴ. 10፥26፤ ሉቃ. 12፥2።እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። 23የሚሰማ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” 24#ማቴ. 7፥2፤ ሉቃ. 6፥38።አላቸውም “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ ለእናንተም ይጨመርላችኋል። 25#ማቴ. 13፥12፤ 25፥29፤ ሉቃ. 19፥26።ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።”
የሚያድገው ዘር ምሳሌ
26እርሱም እንዲህ አለ፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት፤ 27ሌሊትና ቀን ይተኛልም፤ ይነሣልም፤ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድግማል። 28ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች። 29#ኢዩ. 3፥13።ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷአልና ወዲያው ማጨድ ይጀምራል።”
ስለ ሰናፍጭ ዘር ምሳሌ
(ማቴ. 13፥31-34፤ ሉቃ. 13፥18-19)
30እርሱም እንዲህ አለ፥ “የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን እናስመስላታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንመስላታለን? 31እንደ ሰናፍጭ ቅንጣት ናት፤ እርሷም በምድር በተዘራች ጊዜ በምድር ካለ ዘር ሁሉ ታንሳለች፤ 32በተዘራችም ጊዜ ትወጣለች፤ ከአትክልትም ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ የሰማይ ወፎችም በጥላዋ ሊሰፍሩ እስኪችሉ ታላላቅ ቅርንጫፎች ታወጣለች።”
33መስማትም በሚችሉበት መጠን እነዚህን በሚመስል በብዙ ምሳሌ ቃሉን ይነግራቸው ነበር፤ ያለ ምሳሌ ግን አልነገራቸውም፤ 34ለብቻቸውም ሲሆኑ ነገሩን ሁሉ ለገዛ ደቀመዛሙርቱ ይፈታላቸው ነበር።
ኢየሱስ የባሕሩን ማዕበል ጸጥ እንዳደረገ
(ማቴ. 8፥23-27፤ ሉቃ. 8፥22-25)
35በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ “ወደ ማዶ እንሻገር፤” አላቸው። 36ሕዝቡንም ትተው በታንኳዪቱ ውስጥ እንዳለ ወሰዱት፤ ሌሎች ታንኳዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 37ብርቱ ዐውሎ ነፋስም ተነሣና ውሃ በታንኳይቱ እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ በታንኳይቱ ይገባ ነበር። 38እርሱም በስተኋላዋ ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ ቀስቅሰውትም “መምህር ሆይ! ስንጠፋ አይገድህምን?” አሉት። 39ነቅቶም ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ዝም በል፤ ፀጥ በል፤” አለው። ነፋሱም ተወ፤ ታላቅ ፀጥታም ሆነ። 40“እንዲህ የምትፈሩት ስለምን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?” አላቸው። 41እጅግም ፈሩና “እንዲህ ነፋስም ባሕርም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ