የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የማርቆስ ወንጌል 5

5
ኢየሱስ ርኩስ መንፈስ ያደረበትን ሰው እንደ ፈወሰ
(ማቴ. 8፥28-34ሉቃ. 8፥26-39)
1ከባሕሩ ማዶ ተሻግረው ጌርጌሴኖን ወደ ተባለ አገር መጡ። 2ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፥ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጣና ወደ እርሱ መጣ። 3ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። 4ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፥ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያረጋጋው የሚችል አልነበረም። 5በመቃብሮቹና በተራራዎቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኸ ሰውነቱን በድንጋይ ይቆራርጥ ነበር። 6ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ 7በታላቅ ድምፅ ጮኾም፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው። 8ይህንንም ያለው፥ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው። 9ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን#5፥9 “ሌጌዎን” ማለት ጭፍራ ወይም ሠራዊት ማለት ነው። ነው፤” አለው፤ 10ከሀገር ውጭ እንዳያባርራቸው አጥብቆ ለመነው። 11በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ይሰማራ ነበርና፤ 12ኢየሱስን፥ “ወደ አሣማዎቹ እንድንገባ ስደደን፤” ብለው ለመኑት። 13እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡ፤ ሁለት ሺህ ያህል ዐሣማዎችም በርግገው ከገደሉ አፋፍ ወደ ባሕሩ ተወረወሩ፤ በባሕሩ ውስጥም ሰጠሙ።
14እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ በከተማና በገጠርም አወሩ፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት መጡ። 15ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፥ የአጋንንት ሠራዊት አድረውበት የነበረው ሰው፥ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ተቀምጦ አዩት፤ ፍርሃትም አደረባቸው። 16ይህንን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ለያዘው ሰው የሆነውንና በአሳማዎቹም የተደረገውን አወሩ። 17ከዚያም ሀገራቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር። 18ኢየሱስም ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፥ በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር አብሮት ለመሆን ለመነው። 19ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ይልቁን፥ “ወደ ቤትህ ወደ ዘመዶችህም ሂድ፤ ጌታም ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ምሕረት እንዳሳየህ ንገራቸው” አለው። 20እርሱም ሄደ፤ ኢየሱስም ያደረገለትን ነገር “ዐሥር ከተማ” በተባለው አገር በየስፍራው ያበስር ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።
የኢያኢሮስ ልጅና ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት
(ማቴ. 9፥18-26ሉቃ. 8፥40-56)
21ኢየሱስ እንደገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፥ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩም አጠገብ እንዳለ፤ 22ከምኲራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው፥ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፥ 23“ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። 24ኢየሱስም አብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም እያጨናነቀው ተከተለው።
25ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ 26#ጦቢ. 2፥10።በብዙ ባለ መድኀኒቶችም ዘንድ ብዙ ተሠቃይታ፥ ያላትን ሁሉ ጨረሰች እንጂ አልተሻላትም ነበር፤ እንዲያውም ሕመሙ ብሶባት ነበር። 27ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፥ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ 28ምክንያቱም፥ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን እንኳ ብነካ ይፈውሰኛል” በማለት ነበር። 29የሚፈሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ እንደዳነች በሰውነቷ ታወቃት። 30ኢየሱስም ወዲያውኑ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዞሮ፥ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። 31ደቀ መዛሙርቱም፥ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን? አሉት።” 32እርሱም ይህን ያደረገችው ማን እንደ ሆነች ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። 33ሴትዮዋም የተደረገላትን በማወቅዋ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። 34እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ” አላት።
35ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፥ ሰዎች ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥተው የምኵራብ አለቃውን፥ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። 36ኢየሱስ ግን ሰዎቹ ያሉትን ቢሰማም የምኵራቡ ን አለቃ፥ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። 37ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት በደረሱ ጊዜ፥ ሲታወኩ፥ ሰዎቹም ሲያለቅሱና አምርረውም ሲጮኹ ተመለከተ። 39ወደ ውስጥ ገብቶም፥ “ይህን ያህል ለምን ትታወካላችሁ ለምን ታለቅሳላችሁ? ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። 40ሰዎቹም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጣ፤ የልጅቱንም አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን አስከትሎ ልጅቱ ወዳለችበት ገባ። 41ከዚያም የልጅቱን እጅ ይዞ፥ “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ትርጉሙም፥ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። 42ልጅቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ መራመድ ጀመረች፤ ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ ሰዎቹም እጅግ በመደነቅ ተደመሙ። 43እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ