ትንቢተ ናሆም 2

2
1እነሆ፥ መልካም ዜና የሚያመጣ፥ ሰላምንም የሚያሰማ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ በዓሎችሽን አክብሪ፥ ስእለቶችሽን ክፈዪ፤ አጥፊው ፈጽሞ ተቆርጧልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንቺ በኩል አያልፍምና።
የክፉዋ ከተማ ውድቀት
2የሚበትን ከፊት ለፊትሽ መጥቷል፤ ምሽጉን ጠብቂ፥ መንገዱን በደንብ ጠብቂ፤ ወገብሽን አጽኚ፥ ኃይልሽንም እጅግ አበርቺ። 3ጌታ የያዕቆብን ክብር እንደ እስራኤል ክብር ይመልሳል፤ አጥፊዎች አጥፍተዋቸዋልና፥ የወይናቸውን ቅርንጫፎች አጥፍተዋልና። 4የጦረኞቹ ጋሻ ቀልቶአል፥ ኃያላን ሰዎችም ቀይ ልብስ ለብሰዋል። እርሱ በሚያዘጋጅበት ቀን ሰረገሎች እንደ እሳት ይንቦገቦጋሉ፥ ጦሮቹም ይወዘወዛሉ። 5ሰረገሎች በመንገድ ላይ ይከንፋሉ፥ በአደባባዮችም ወዲህና ወዲያ ይጣደፋሉ፤ መልካቸው እንደ ፋና ነው፥ እንደ መብረቅም ይወረወራሉ። 6መሳፍንቱን ያስባል፤ በአረማመዳቸው ይሰናከላሉ፤ ፈጥነው ወደ ቅጥርዋ ይሮጣሉ፥ መጠለያም ተዘጋጅቷል። 7የወንዞቹ በሮች ተከፈቱ፥ ቤተ መንግሥቱም ቀለጠ። 8ቆሟል፥ ተገለጠች፥ ተማረከች፥ ሴቶች አገልጋዮቿም እንደ ርግብ እየጮኹና ደረታቸውን እየመቱ አለቀሱ።
9ነነዌ በዘመኗ ሁሉ እንደ ተከማቸ ውኃ ነበረች፤ እርሱም እየደረቀ ነው። “ቁሙ፥ ቁሙ” ይላሉ፥ ነገር ግን የሚመለስ የለም። 10ብሩን በዝብዙ፥ ወርቁንም በዝብዙ፤ ሃብቷ ማለቂያ የለውምና፥ የከበረው የዕቃዋ ሁሉ ብዛት አይቆጠርምና። 11ባዶ፥ ባድማና የጠፋች ሆናለች፥ ልብ ቀልጦአል፥ ጉልበቶች ተብረክርከዋል፤ በወገብም ሁሉ ሕማም አለ፥ የሁሉም ፊት ጠቁሮአል። 12አሁን ታድያ የአንበሶቹ ዋሻ፥ ደቦሎቻቸውን ያበሉበት፥ ወንዱና ሴቷ አንበሳ የሄዱበት፥ ግልገሎቹም ሳይፈሩ የተሰማሩበት ወዴት ነው? 13አንበሳው ለልጆቹ የሚበቃውን ያህል ነጠቀ፥ ለእንስቶቹም አነቀላቸው፥ ዋሻውን በነጠቀው፥ ጉድጓዱንም በተቦጫጨቀ ሥጋ ሞልቶታል። 14እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ሰረገሎችዋን አቃጥዬ አጨሰዋለሁ፥ የአንበሳ ደቦሎችሽን ሰይፍ ይበላቸዋል፤ ንጥቂያሽን ከምድር አጠፋለሁ፥ የመልዕክተኞችሽ ድምፅ ዳግም አይሰማም።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ