የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 16

16
ቆሬ ዳታንና አቤሮን ማመፃቸው
1 # ሲራ. 45፥18-20። # ይሁዳ 1፥11። የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ የኤልያብ ልጆች ዳታንንና አቤሮንን ከሮቤልም ልጆች የፋሌት ልጅ ኦንን ወሰዳቸው። 2ከእስራኤልም ልጆች ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች የሆኑ ከጉባኤው የተመረጡ፥ በዝናቸውም የገነኑ የማኅበሩ አለቆች ጋር በመሆን እነርሱ በሙሴ ላይ ተነሡ። 3በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ ጌታም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችሁታል፤ በጌታም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?”
4ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወድቆ ሰገደ፤ 5ለቆሬም እርሱንም ለተከሉት ሁሉ እንዲህ ቡሎ ተናገረ፦ “ነገ ጠዋት ጌታ ለእርሱ የሆነውን ሰው፥ ቅዱስም ማን እንሆነ፥ ወደ እርሱም ለመቅረብ የተፈቀደለትን ሰው ያሳውቃል፤ የመረጠውንም ሰው ወደ እርሱ እንዲቀርብ ይፈቅድለታል። 6እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና እርሱንም የተከተሉት ሁሉ፥ ጥናዎችን ይውሰዱ፤ 7በማግስቱም በጌታ ፊት እሳት አድርጉባቸው፥ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እንዲህም ይሆናል፤ ጌታ የሚመርጠው እርሱ ቅዱስ ይሆናል፤ እናንተ የሌዊ ልጆች ሆይ! እጅግ አብዝታችሁታል።” 8ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፦ “እናንተ የሌዊ ልጆች፥ እባካችሁ ስሙ፤ 9የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር የለያችሁ፥ የጌታንም ማደሪያ አገልግሎት እንድትሠሩ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት እንድትቆሙ ወደ እርሱ ለማቅረብ መፍቀዱን እንደ ቀላል ነገር ቈጠራችሁትን? 10አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ እንድትቀርቡ ፈቅዶላችኋል፤ ታዲያ አሁን ደግሞ ክህነትንም ትፈልጋላችሁን? 11ስለዚህም አንተና አንተንም የሚከተሉህ ሁሉ በጌታ ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ የምታጉረመርሙት አሮን ማን ስለ ሆነ ነው?”
12ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም እንዲህ አሉ፦ “አንመጣም፤ 13እኛን በምድረ በዳ ለመግደል ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን ቀላል እንደሆነ ነገር ቈጠርከውን? እንዲሁም በእኛ ላይ ራስህን ፈጽሞ አለቃ ታደርጋለህን? 14ደግሞስ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አላስገባኸንም፥ እርሻና የወይንም ተክል ቦታ አላወረስከንም፤ የእነዚህንስ ሰዎች ዐይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም።”
15ሙሴም እጅግ ተቈጣ፥ ጌታንም እንዲህ አለው፦ “ወደ ቁርባናቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንድ አህያ እንኳ አልወሰድሁም፥ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም።” 16ሙሴም ቆሬን እንዲህ አለው፦ “ነገ አንተ፥ አንተንም የሚከተሉህ ሁሉ፥ አሮንም በጌታ ፊት ተገኙ፤ 17ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፥ ዕጣንም አድርጉባቸው፥ እያንዳንዳችሁም ጥናዎቻችሁን ወደ ጌታ ፊት አምጡ፥ ሁለት መቶ ኀምሳ ጥናዎች፤ አንተም እንዲሁም አሮን እያንዳንዳችሁ ጥናዎቻችሁን አምጡ።” 18እያንዳንዳቸውም ጥናቸውን ወሰዱ፥ እሳትም አደረጉባቸው፥ ዕጣንም ጨመሩባቸው፥ ከሙሴና ከአሮንም ጋር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቆሙ። 19ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የጌታም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ።
20ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 21“ሁሉንም በአንድ ጊዜ ስለማጠፋቸው ከዚህ ማኅበር መካከል ተለዩ።” 22እነርሱም በግምባራቸው ወድቀው በመስገድ እንዲህ አሉ፦ “አምላክ ሆይ! አንተ የሥጋ ለባሽ ሁሉ መንፈስ አምላክ፥ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ አንተ በማኅበሩ ሁሉ ላይ ትቈጣለህን?” 23ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24“ለማኅበሩ እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ዙሪያ ርቃችሁ ገለል በሉ።”
25ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ተከተሉት። 26እርሱም ለማኅበሩ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦ “እባካችሁ፥ ከእነዚህ ክፉዎች ድንኳን ርቃችሁ ገለል በሉ፤ በኃጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ የእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ።” 27ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማደሪያ ከዙሪያውም ሁሉ ርቀው ገለል አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ሚስቶቻቸውም ልጆቻቸውም ሕፃናቶቻቸውም ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ። 28ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ይህን ሥራ ሁሉ ለመሥራት ጌታ ልኮኛል እንጂ ከልቤ አስቤው እንዳልሆነ በዚህ ታውቃላችሁ። 29እነዚህ ሰዎች በተፈጥሮ ሰው እንደሚሞተው ቢሞቱ፥ ወይም ሰው ሁሉ እንደሚቀበለው የዕጣ ክፍሉ የሚቀበሉ ቢሆን እኔን ጌታ አልላከኝም። 30ጌታ ግን አንድ አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያንጊዜ እነዚህ ሰዎች ጌታን እንደ ናቁ ታውቃላችሁ።”
31እንዲህም ሆነ፤ እነዚህን ቃላት ሁሉ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ ከበታቻቸው ያለው መሬት ተሰነጠቀ፤ 32ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ የቆሬም የሆኑትን ሰዎች ሁሉ፥ ዕቃዎቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። 33እነርሱም የእነርሱም የሆነው ሁሉ በሕይወታቸው ሳሉ ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ላይ ተዘጋችባቸው፥ ከጉባኤውም መካከል ጠፉ። 34“ምድሪቱ እኛንም ደግሞ እንዳትውጠን” ብለው በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ከእነርሱ ጩኸት የተነሣ ሸሹ። 35እሳትም ከጌታ ዘንድ ወጥቶ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች በላቸው።
36ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 37“ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ተናገር፦ የተቀደሱ ናቸውና ጥናዎቹን ከሚነድደው እሳት መከካከል ውሰድ፥ እሳቱንም ወደ ውጭ አርቀህ በትነው፤ 38በኃጢአታቸው የተነሣ ሕይወታቸውን አሳልፈው ለሞት የሰጡትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፋችሁ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጓቸው፤ በጌታ ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።” 39ካህኑም አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወሰደ፤ እነርሱንም ጠፈጠፏቸው ለመሠዊያው መለበጫ አደረጓቸው። 40በቆሬና በእርሱም ተከታዮች ላይ የደረሰው እንዳይደርስበት፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በጌታ ፊት ዕጣንን ለማጠን እንዳይቀርብ፥ ጌታ በሙሴ እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው።
41በማግስቱም የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ፦ “እናንተ የጌታን ሕዝብ ገድላችኋል” ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። 42እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ ወደ መገናኛው ድንኳን ዘወር ብለው ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈነው፥ የጌታም ክብር ተገለጠ። 43ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ወዳለው ስፍራ መጡ። 44#ጥበ. 18፥20-25።ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 45“ከዚህ ማኅበር መካከል ርቃችሁ ገለል በሉ፥ እኔም በአንድ ጊዜ አጠፋቸዋለሁ።” በግምባራቸውም ወድቀው ሰገዱ። 46ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፦ “ጥናህን ውሰድ፥ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፥ ዕጣንም ጨምርበት፥ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው አስተስርይላቸውም፤ ከጌታ ዘንድ ቁጣ ወጥቶአልና መቅሠፍት ጀምሮአል።” 47አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ጉባኤው መካከል ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፥ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው። 48በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተገታ። 49በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 50መቅሠፍቱም በተገታ ጊዜ አሮን ወደ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ