የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኍልቊ 26

26
የአዲሱ ትውልድ የሕዝብ ቆጠራ
1 # ዘኍ. 1፥1-46። እንዲህም ሆነ፤ መቅሠፍቱ ከሆነ በኋላ ጌታ ሙሴንና የካህኑን የአሮን ልጅ አልዓዛርን እንዲህ አላቸው፦ 2“ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን፥ በእስራኤል ወደ ጦርነት የሚወጣውን ሁሉ፥ የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ በየአባቶቻቸው ቤት ቁጠሩ።” 3ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ላይ እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ 4ጌታ ሙሴን እንዳዘዘው “ዕድሜው ሀያ ዓመት የሆነውንና ከዚያም በላይ ያለውን ሕዝብ ቁጠሩ።” ከግብጽም ምድር የወጡት የእስራኤል ልጆች እነዚህ ነበሩ፦
5የእስራኤል በኩር ሮቤል፤ የሮቤልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሄኖኅ የሄኖኀውያን ወገን፥ ከፈሉስ የፈሉሳውያን ወገን፥ 6ከአስሮን የአስሮናውያን ወገን፥ ከከርሚ የከርማውያን ወገን። 7እነዚህ የሮቤላውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 8የፈሉስም ልጆች፤ ኤልያብ። 9የኤልያብም ልጆች፤ ነሙኤል፥ ዳታን፥ አቤሮን ናቸው፤ እነዚህ ዳታንና አቤሮን ከማኅበሩ የተመረጡ ነበሩ፤ ቆሬን ከተከተሉት ሰዎች ጋር በመሆን በጌታ ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን የተገዳደሩ ነበሩ፤ 10ያም ወገን በሞተ ጊዜ፥ እሳቲቱም ሁለት መቶ ኀምሳውን ሰዎች ባቃጠለች ጊዜ ምድሪቱ አፍዋን ከፍታ እነርሱን ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ እነርሱም ለምልክት ሆኑ። 11የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም።
12በየወገናቸው የስምዖን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከነሙኤል የነሙኤላውያን ወገን፥ ከያሚን የያሚናውያን ወገን፥ ከያኪን የያኪናውያን ወገን፥ 13ከዛራ የዛራውያን ወገን፥ ከሳኡል የሳኡላውያን ወገን። 14እነዚህ የስምዖናውያን ወገኖች ናቸው፤ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
15በየወገናቸው የጋድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከጽፎን የጽፎናውያን ወገን፥ ከሐጊ የሐጋውያን ወገን፥ ከሹኒ የሹናውያን ወገን፥ 16ከኤስናን የኤስናናውያን ወገን፥ ከዔሪ የዔራውያን ወገን፥ 17ከአሮድ የአሮዳውያን ወገን፥ ከአርኤሊ የአርኤላውያን ወገን። 18እነዚህ የጋድ ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
19የይሁዳ ልጆች ዔርና አውናን ናቸው፤ ዔርና አውናንም በከነዓን ምድር ሞቱ። 20በየወገናቸው የይሁዳም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሴሎም የሴሎማውያን ወገን፥ ከፋሬስ የፋሬሳውያን ወገን፥ ከዛራ የዛራውያን ወገን። 21የፋሬስም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከኤስሮም የኤስሮማውያን ወገን፥ ከሐሙል የሐሙላውያን ወገን። 22እነዚህ የይሁዳ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
23በየወገናቸው የይሳኮር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከቶላ የቶላውያን ወገን፥ ከፉዋ የፉዋውያን ወገን፥ 24ከያሱብ የያሱባውያን ወገን፥ ከሺምሮን የሺምሮናውያን ወገን። 25እነዚህ የይሳኮር ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስልሳ አራት ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
26በየወገናቸው የዛብሎን ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከሴሬድ የሴሬዳውያን ወገን፥ ከኤሎን የኤሎናውያን ወገን፥ ከያሕልኤል የያሕልኤላውያን ወገን። 27እነዚህ የዛብሎናውያን ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ስልሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
28በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ምናሴና ኤፍሬም። 29የምናሴ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከማኪር የማኪራውያን ወገን፤ ማኪርም ገለዓድን ወለደ፤ ከገለዓድ የገለዓዳውያን ወገን። 30የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከኢዔዝር የኢዔዝራውያን ወገን፥ ከኬሌግ የኬሌጋውያን ወገን፥ 31ከአሥሪኤል የአሥሪኤላውያን ወገን፥ ከሴኬም የሴኬማውያን ወገን፥ 32ከሸሚዳ የሸሚዳውያን ወገን፥ ከኦፌር የኦፌራውያን ወገን። 33የኦፌርም ልጅ ሰለጰአድ ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዓድም የሴቶች ልጆቹ ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ። 34እነዚህ የምናሴ ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ኀምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
35በየወገናቸው የኤፍሬም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሱቱላ የሱቱላውያን ወገን፥ ከቤኬር የቤኬራውያን ወገን፥ ከታሐን የታሐናውያን ወገን። 36እነዚህ የሱቱላ ልጆች ናቸው፤ ከዔዴን የዔዴናውያን ወገን። 37እነዚህ የኤፍሬም ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ልጆች እነዚህ ናቸው።
38በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከቤላ የቤላውያን ወገን፥ ከአስቤል የአስቤላውያን ወገን፥ ከአኪራን የአኪራናውያን ወገን፥ 39ከሶፋን የሶፋናውያን ወገን፥ ከሑፋም የሑፋማውያን ወገን። 40እነዚህ የቤላም ልጆች ናቸው፤ አርድና ናዕማን፤ ከአርድ የአርዳውያን ወገን፥ ከናዕማን የናዕማናውያን ወገን። 41በየወገናቸው የብንያም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
42በየወገናቸው የዳን ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከሰምዔ የሰምዔያውያን ወገን፤ በየወገናቸው የዳን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 43የሰምዔያውያን ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩት ስልሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
44በየወገናቸው የአሴር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከዪምና የዪምናውያን ወገን፥ ከየሱዋ የየሱዋውያን ወገን፥ ከበሪዓ የበሪዓውያን ወገን። 45እነዚህ ከበሪዓ ልጆች ናቸው፤ ከሔቤር የሔቤራውያን ወገን፥ ከመልኪኤል የመልኪኤላውያን ወገን። 46የአሴርም የሴት ልጁ ስም ሤራሕ ነበረ። 47እነዚህ የአሴር ልጆች ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
48በየወገናቸው የንፍታሌም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ከያሕጽኤል የያሕጽኤላውያን ወገን፥ ከጉኒ የጉናውያን ወገን፥ 49ከዬጽር የዬጽራውያን ወገን፥ ከሺሌም የሺሌማውያን ወገን። 50በየወገናቸው የንፍታሌም ወገኖች እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
51ከእስራኤል ልጆች የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ።
52 # ዘኍ. 34፥13፤ ኢያ. 14፥1፤2። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 53“ለእነዚህ እንደየስማቸው ቍጥር መጠን ምድሪቱ ርስት ሆና ትከፋፈላለች። 54በየወገናቸው ለብዙዎቹ እንደ ብዛታቸው፥ ለጥቂቶቹም እንደ ጥቂትነታቸው መጠን ርስትን ትሰጣቸዋለህ። ለሁሉ እንደ ቁጥራቸው መጠን ርስታቸው ይሰጣቸዋል። 55ነገር ግን ምድሪቱ በዕጣ ትከፋፈላለች፤ እንደ አባቶቻቸው ነገድ ስም ይወርሳሉ። 56በብዙዎችና በጥቂቶች መካከል ርስታቸው በዕጣ ትከፋፈላለች።”
57ከሌዋውያንም በየወገናቸው የተቈጠሩት እነዚህ ናቸው፤ ከጌድሶን የጌድሶናውያን ወገን፥ ከቀዓት የቀዓታውያን ወገን፥ ከሜራሪ የሜራራውያን ወገን። 58እነዚህ የሌዊ ወገኖች ናቸው፤ የሊብናውያን ወገን፥ የኬብሮናውያን ወገን፥ የሞሖላውያን ወገን፥ የሙሳውያን ወገን፥ የቆሬያውያን ወገን። ቀዓትም እንበረምን ወለደ። 59የእንበረም ሚስት ስም ዮካብድ ነበረ። እርሷ በግብጽ ከሌዊ የተወለደች የሌዊ ልጅ ነበረች፤ ለእንበረምም አሮንንና ሙሴን እኅታቸውንም ማርያምን ወለደችለት። 60#ዘኍ. 3፥2።ለአሮንም ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ተወለዱለት። 61#ዘሌ. 10፥1፤2፤ ዘኍ. 3፥4።በጌታም ፊት ያልተፈቀደውን እሳት ባቀረቡ ጊዜ ናዳብና አብዩድ ሞቱ። 62ዕድሜአቸው አንድ ወር የሞላቸውና ከዚያም በላይ ያሉት ወንዶች ሁሉ ከእነርሱ የተቈጠሩ ሀያ ሦስት ሺህ ነበሩ። ከእስራኤልም ልጆች መካከል ርስት አልተሰጣቸውምና ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም።
63በሞዓብ ሜዳ ላይ በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት ሲቈጠሩ፥ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር የቈጠሩአቸው የእስራኤል ልጆች እነዚህ ናቸው። 64ነገር ግን ሙሴና ካህኑ አሮን በሲና ምድረ በዳ የእስራኤልን ልጆች በቈጠሩአቸው ጊዜ ከነበሩት ከእነዚያ መካከል አንድም ሰው አልነበረም። 65#ዘኍ. 14፥26-35።ጌታ ስለ እነርሱ፦ “በእውነት በምድረ በዳ ይሞታሉ” ብሎ ተናግሮአልና። ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ ከነዌም ልጅ ከኢያሱ በቀር ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ አልቀረም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ