ኦሪት ዘኍልቊ 3
3
የአረሮን ልጆች
1ጌታም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። 2#ዘኍ. 26፥60።እነዚህ የአሮን ልጆች ስሞች ናቸው፤ በኩሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። 3የአሮን ልጆች፥ እርሱም በክህነት አገልግሎት እንዲያገለግሉ የቀደሳቸው፥ የተቀቡ ካህናት ስሞቻቸው እነዚህ ናቸው። 4#ዘሌ. 10፥1፤2፤ ዘኍ. 26፥61።ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በጌታ ፊት ያልተፈቀደውን እሳት ባቀረቡ ጊዜ በጌታ ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር።
የሌዋውያን ግዴታዎች
5ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6“የሌዊን ነገድ አምጥተህ አቅርብ እንዲያገለግሉትም በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። 7የማደሪያውንም ሥራ እየሠሩ፥ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለእርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ያለባቸውን ግዴታዎች ይፈጽሙ። 8የማደሪያውንም ሥራ እየሠሩ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቃሉ፥ ለእስራኤልንም ልጆች ያለባቸውን ግዴታ ይወጣሉ። 9ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለእርሱ ፈጽሞ የተሰጡ ናቸው። 10አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ማናቸውም ሌላ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።”
11ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12#ዘፀ. 13፥2።“እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኩሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤ ሌዋውያንም የእኔ ናቸው፥ 13ምክንያቱም በኩር ሁሉ የእኔ ነውና፤ በግብጽ ምድር በኩርን ሁሉ በገደልሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኩርን ሁሉ፥ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ያለውን ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሆናሉ። እኔ ጌታ ነኝ።”
በሌዋውያን ላይ የተደረገ የሕዝብ ቈጠራ
14ጌታም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 15“የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቁጠር፤ ወንዱን ሁሉ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውንና ከዚያም በላይ ያለውን ቁጠራቸው።” 16ሙሴም እንደ ጌታ ቃል፥ እንደ ታዘዘው ቈጠራቸው። 17በየስማቸውም የሌዊ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 18የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ። 19የቀዓትም ልጆች በየወገኖቻቸው፤ እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል። 20የሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው።
21በጌድሶን ውስጥ የሎቤናውያን ወገንና የሰሜአውያን ወገን ይካተቱ ነበር፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 22ከእነርሱ የተቈጠሩት ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የወንዶች ሁሉ ቍጥር ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ። 23የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በስተጀርባ በምዕራብ በኩል ይሰፍራሉ። 24የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። 25ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያውን፥ ድንኳኑን፥ መደረቢያውን፥ የመገናኛውንም ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ 26የአደባባዩንም መጋረጆች፥ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፥ ገመዶቹንም መገልገያውንም ሁሉ ይሆናል።
27በቀዓት ውስጥም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ይካተቱ ነበር፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 28ወንዶች ሁሉ እንደ ቁጥራቸው ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ የመቅደሱንም ግዴታ ለመፈጸም የተዘጋጁ ነበሩ። 29የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ። 30የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል። 31ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ ካህናቱም የሚገለገሉባቸውን የመቅደሱን ዕቃዎች፥ መጋረጃውንም፥ መገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ። 32የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም የመቅደሱን ግዴታ በሚፈጽሙት ላይ ተቆጣጣሪ ይሆናል።
33በሜራሪ ውስጥ የሞሖላውያን ወገንና የሙሳያውያን ወገን ይካተቱ ነበር፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው። 34ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቁጥራቸው ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 35የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ እነርሱም በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ። 36የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያውን ሳንቆች፥ መቀርቀሪያዎቹንም፥ ምሶሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ ዕቃዎቹንም ሁሉ መገልገያውንም ሁሉ፥ 37በዙሪያውም የሚቆሙትን የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ አውታሮቹንም ይሆናል።
38በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ በመቅደሱም ውስጥ ማናቸውንም ለእስራኤል ልጆች የሚደረገውን ሥርዓት ይጠብቃሉ፤ ማናቸውም ልዩ ሰው ግን ቢቀርብ ይገደል።
39በጌታ ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ።
በኩርን መቤዠት
40ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤልን ልጆች የወንድ በኩር ሁሉ ቁጠር፤ ዕድሜቸው አንድ ወር የሞላቸውንና ከዚያም በላይ ያሉትን በየስማቸው ቈጥረህ ቁጥሩን ውሰድ፤ 41ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኩር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ትወስዳለህ፥ እኔ ጌታ ነኝ።” 42ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኩር ሁሉ ቈጠረ። 43ከእነርሱም የተቈጠሩ የወንድ በኩር ሁሉ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የተቈጠሩት ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ።
44ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 45“ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም የእኔ ናቸው፤ እኔ ጌታ ነኝ። 46ከሌዋውያን ወንዶች ቍጥር በላይ የሆኑትን ሁለት መቶ ሰባ ሦስት የእስራኤል ልጆች በኵራትን ለመዋጀት፥ 47ለእያንዳንዱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው። 48ከቍጥር በላይ የሆኑት የተዋጁበትን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” 49ሙሴም በሌዋውያን ከተዋጁት ቍጥር በላይ ከሆኑት ዘንድ የመዋጃውን ገንዘብ ወሰደ። 50ከእስራኤል ልጆች በኵራት አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ገንዘቡን ወሰደ። 51ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ጌታ ቃል፥ ሙሴ የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ