ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2
2
የክርስቶስ ትሕትና ምሳሌነት
1ስለዚህ ለእናንተ በክርስቶስ አንዳች መበረታተታት ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናትም ቢሆን፥ የመንፈስም ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄም ቢሆኑ፥ 2በአንድ አሳብ ተስማምታችሁና አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። 3ከራስ ወዳድነት ወይም ከትምክሕት የተነሣ አንድም ነገር አታድርጉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በትሕትና ባልንጀራውን ከራሱ ይልቅ እንደሚሻል አድርጎ ይቁጠር፤ 4እያንዳንዱም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ። 5በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይኑር። 6እርሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ ኖሮት ሳለ እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር እኩልነትን እንደመንጠቅ አድርጎ አልቈጠረውም፤ 7ነገር ግን እንደ ሰው ሆኖ በመወለድ የባርያን መልክ ይዞ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በሰው አምሳል ተገኝቶ፥ 8በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመቀበል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። 9በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከስምም ሁሉ የሚበልጠውን ስም ሰጠው፤ 10#ኢሳ. 45፥23።በዚህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም እንዲንበረከኩና 11መላስ ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር እንዲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ እንዲመሰክሩ ነው።
ለዓለም ብርሃን መሆን እንደሚገባ
12ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ! ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ ይበልጥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ 13በጎ ፈቃዱን እንድትፈልጉና እንድታደርጉ ሁለቱንም በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።
14ሁሉንም ነገሮች ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤ 15#ዘዳ. 32፥5።በዚህም በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ሆናችሁ በዚህ ዓለም እንደ ከዋክብት የምታበሩ፥ ያለ ነቀፋ የዋሆችና ነውርም የሌለባችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆናላችሁ፤ 16እናንተም የሕይወትን ቃል በጽኑ በመያዛችሁ ምክንያት በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ነገር ይሆንልኛል። 17ነገር ግን በእምነታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስስ ደስ ይለኛል፤ ከእናንተም ከሁላችሁ ጋር አብሬ ሐሤት አደርጋለሁ፤ 18እናንተም ደግሞ እንዲሁ ደስ ይበላችሁ፤ ከእኔም ጋር አብራችሁ ሐሤት አድርጉ።
የጢሞቴዎስና የኤጳፍሮዲጡስ ለአገልግሎት መላክ
19ነገር ግን ስለ እናንተ ባወቅሁ ጊዜ ደስ ተሰኝቼ እንድበረታታ ፈጥኜ ጢሞቴዎስን ልልክላችሁ በጌታ በኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ። 20እንደ እኔ ሆኖ ስለ ደኅንነታችሁ በቅንነት የሚጨነቅ እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝምና፤ 21የተቀሩት ሁሉ ግን የክርስቶስ ኢየሱስን ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም የሚሹ ናቸውና። 22ነገር ግን ጢሞቴዎስ ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል በማገልገል መፈተኑን ታውቃላችሁ። 23እንግዲህ በእኔ ዘንድ ያለውን ሁኔታ አይቼ፥ እርሱን ቶሎ እንደምልክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ 24እኔም ራሴ ደግሞ ፈጥኜ እንደምመጣ በጌታ ታምኜአለሁ።
25ነገር ግን ወንድሜንና ከእኔ ጋር አብሮ ሠራተኛና ወታደር፥ የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን ኤጳፍሮዲጡስን ወደ እናንተ መላክ ፍጹም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ 26ሁላችሁን ይናፍቃልና፤ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል። 27በእርግጥ በጠና ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበርና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ማረው፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ያደረገው ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ኀዘን በኀዘን ላይ እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ደግሞ ነው። 28እንግዲህ እንደገና ስታዩት ደስ እንዲላችሁ ለእኔም ኀዘኔ እንዲቃለል በተቻለ ፍጥነት ወደ እናንተ እልከዋለሁ። 29እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ 30ምክንያቱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለመፈጸም ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ለክርስተቶስ ሥራ ሲል ለሞት ተቃርቦ ነበርና።
Currently Selected:
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ