የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 15

15
1የለዘበች መልስ ቁጣን ትመልሳለች፥
ሸካራ ቃል ግን ቁጣን ታስነሣለች።
2የጠቢባን ምላስ እውቀትን ያሳምራል፥
የሰነፎች አፍ ግን ስንፍናን ያፈልቃል።
3የጌታ ዐይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፥
ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ።
4ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፥
የጠማማ ምላስ ግን ነፍስን ይሰብራል።
5ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፥
ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው።
6በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ፥
የኀጥእ ሰው መዝገብ ግን ሁከት ነው።
7የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች፥
የሰነፎች ልብ ግን እንዲህ አይደለም።
8የኀጥኣን መሥዋዕት በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥
የቅኖች ጸሎት ግን በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው።
9የኀጥኣን መንገድ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ነው፥
እርሱ ግን ጽድቅን የሚከተል ይወድዳል።
10ክፉ መቅሠፍት መንገድን በተወ ሰው ላይ ይመጣል፥
ዘለፋንም የሚጠላ ይሞታል።
11ሲኦልና ጥፋት በጌታ ፊት የታወቁ ናቸው፥
ይልቁንም የሰዎች ልብ የታወቀ ነው።
12ፌዘኛ ሰው የሚዘልፈውን አይወድድም፥
ወደ ጠቢባንም አይሄድም።
13ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል፥
በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች።
14የአዋቂ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፥
የሰነፎች አፍ ግን በስንፍና ይሰማራል።
15ልቡ የሚያዝን ሰው ዘመኑ ሁሉ የከፋች ናት፥
የልብ ደስታ ግን ሁልጊዜ እንደ ግብዣ ነው።
16ጌታን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር
ሁከት ካለበት ከብዙ መዝገብ ይሻላል።
17የጐመን ወጥ በፍቅር መብላት
የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል።
18ቁጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፥
ትዕግሥተኛ ሰው ግን ጸጥ ያሰኘዋል።
19የታካች መንገድ እንደ እሾህ አጥር ናት፥
የጻድቃን መንገድ ግን የተደላደለች ናት።
20ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፥
ሰነፍ ልጅ ግን እናቱን ይንቃል።
21ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፥
አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቀናል።
22ምክር ከሌለች የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፥
መካሮች በበዙበት ግን ይጸናል።
23ሰው በአፉ መልስ ደስ ይለዋል፥
ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!
24በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ
የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል።
25ጌታ የትዕቢተኞችን ቤት ይነቅላል፥
የባልቴትን ዳርቻ ግን ያጸናል።
26የበደለኛ አሳብ በጌታ ዘንድ አስጸያፊ ናት፥
ያማረ ቃል ግን ጥሩ ነው።
27ትርፍ ለማግኘት የሚሳሳ ሰው የራሱን ቤት ያውካል፥
መማለጃን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል።
28የጻድቅ ልብ መልሱን ያስባል፥
የኀጥኣን አፍ ግን ክፋትን ያፈልቃል።
29ጌታ ከኀጥኣን ይርቃል፥
የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል።
30የዐይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል፥
መልካም ወሬም አጥንትን ያለመልማል።
31የሕይወትን ተግሣጽ የሚሰማ ጆሮ
በጠቢባን መካከል ይኖራል።
32ተግሣጽን ቸል የሚል የራሱን ነፍስ ይንቃል፥
ዘለፋን የሚሰማ ግን አእምሮ ያገኛል።
33ጌታን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፥
ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ